የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአሜሪካ አትላንታ ከተማ ከፊታችን ግንቦት 13 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ የመንገደኞች የበረራ አገልግሎት ዳግም እንደሚጀምር ይፋ አድርጓል።
አየር መንገዱ እንዳስታወቀው፣ ከአዲስ አበባ ወደ አትላንታ የሚደረገው ይህ ቀጥታ በረራ በሳምንት ለሦስት ቀናት የሚከናወን ይሆናል።
አትላንታ በአሜሪካ የንግድና የኢንዱስትሪ እንቅስቃሴ ከፍተኛ ስፍራ ያላት፣ በዓለማችን እጅግ ሥራ በሚበዛበት "ሀርትስፊልድ ጃክሰን" ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ መገኛ ናት።
ይህ መዳረሻ በአሜሪካ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ምቹ የአየር ጉዞ አማራጭ ከመሆኑም በላይ፣ አፍሪካን ከሰሜን አሜሪካ ጋር በንግድና በቱሪዝም ይበልጥ ለማስተሳሰር ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል ተብሎ ታምኖበታል።
ከተመሠረተ 80 ዓመታትን ያስቆጠረውና አፍሪካን ከመላው ዓለም ጋር በማገናኘት ረገድ ግንባር ቀደም የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ በረራው ዳግም መጀመሩ በአሁኑ ወቅት በአሜሪካ እያደረገ ያለውን የአገልግሎት ተደራሽነት ይበልጥ ያጠናክረዋል።
አየር መንገዱ በአሁኑ ወቅት ዋሽንግተን ዲሲን፣ ኒውዮርክንና ቺካጎን ጨምሮ በተለያዩ የሰሜን አሜሪካ ከተሞች በረራዎቹን በማስፋፋት ላይ ይገኛል።
በላሉ ኢታላ