Search

ለክልሎች የሚሰጠው የጋራ ገቢ ድርሻ ከ4.2 ቢሊዮን ወደ 91.7 ቢሊዮን ብር አድጓል፡- አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር

ረቡዕ መጋቢት 09, 2018 42

ከጋራ ገቢ ለክልሎች የሚሰጠው የበጀት ድርሻ ከለውጡ በፊት ከነበረበት 4.2 ቢሊዮን ብር በ2017 በጀት ዓመት ወደ 91.7 ቢሊዮን ብር ከፍ ማለቱን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር አስታወቁ።
አፈ ጉባኤው ይህንን የገለጹት ምክር ቤቱ ለአዳማ ከተማ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቋሚ ኮሚቴ አባላት በፊስካል ግንኙነት ዙሪያ ሥልጠና መስጠት በጀመረበት ወቅት ነው።
በኢትዮጵያ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልን ለማረጋገጥ እየተከናወኑ ባሉ ሪፎርሞች ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑ ተመላክቷል።
ፊስካል ፌዴራሊዝም የሀገሪቱን የኢኮኖሚ አንድነት ለመገንባትና ጤናማ ሥርዓት እንዲኖር ለማድረግ የማይተካ ሚና እንዳለውም ተገልጿል።
ምክር ቤቱ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልን የሚያረጋግጡ የሕግ ማዕቀፎችንና የድጎማ በጀት ቀመሮችን በማዘጋጀት ውጤታማ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል።
በተመሳሳይ ከከፍተኛ ማዕድንና ፔትሮሊየም ሀብቶች የሚገኘው የባለቤትነት ክፍያ (ሮያሊቲ) ገቢም ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል።
በ2013 ዓ.ም 11 ሚሊዮን ብር የነበረው ይህ ገቢ፣ በ2017 በጀት ዓመት ከ468 ሚሊዮን ብር በላይ ደርሶ ለክልሎች ተከፋፍሏል።
ከዚህ ቀደም ግልጽ አሠራር ያልነበረው "ውስን ዓላማ ያላቸው ድጎማዎች" አሰጣጥ ሥርዓትም ተዘርግቶለታል። በዚህም መሠረት በ2017 በጀት ዓመት ከ226.18 ቢሊዮን ብር በላይ ለክልልና ከተማ አስተዳደሮች በፍትሐዊነት ተላልፏል።
ፊስካል ፌዴራሊዝም የመንግሥትን የመፈጸም አቅም ለማሳደግና ግልጽነትን ለማስፈን ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው።
በምክር ቤቱ የተዘጋጀው ሥልጠናም የቋሚ ኮሚቴውን የክትትልና ቁጥጥር ሚና ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ተብሏል።
በአባዲ ወይናይ