የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የ2018 ዓ.ም የዒድ አልፈጥር በዓልን ምክንያት በማድረግ ከ100 ሺህ በላይ ወገኖች የማዕድ ማጋራት መርሐ-ግብር አከናወኑ።
በዚህ የማዕድ ማጋራት መርሐ-ግብር የዘይት፣ የዱቄትና የሩዝ ድጋፍ የተደረገላቸው አካላት ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች፣ አቅመ ደካሞች፣ አካል ጉዳተኞችና የሀገር ባለውለታዎች ናቸው።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ እንደገለጹት፤ የከተማ አስተዳደሩ በረመዷን ወር ውስጥ በከተማዋ በሚገኙ 28 የምገባ ማዕከላት ኢፍጣር በማዘጋጀት መልካም ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል። በዚህም በረመዷን ወር ወደ 27 ሺህ የሚጠጉ ወገኖች ፆሙን ሳይቸገሩ እንዲያሳልፉ መደረጉን ተናግረዋል።
"ዛሬ የምናደርገው የማዕድ ማጋራት ለሕዝባችን ያለንን ፍቅርና አክብሮት የምንገልጽበት ነው" ያሉት ከንቲባዋ፤ ልበ ቀና ባለሀብቶችንና ተቋማትን በማስተባበር ለተደረገው ለዚህ ድጋፍ ከንቲባዋ ምስጋና አቅርበዋል።
በተለይም ድጋፉን ላደረጉት ለሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጀማል አህመድና ለተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ኤምባሲ ልዩ ምስጋና አቅርበዋል።
በይመር አደም