Search

ኢትዮጵያና ጣሊያን በልማት ፖሊሲና በታላላቅ ፕሮጀክቶች ዙሪያ ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር ተስማሙ

ረቡዕ መጋቢት 09, 2018 40

በገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ የተመራ የኢትዮጵያ ልዑክ በሮም ከጣሊያን የኢኮኖሚና ፋይናንስ ሚኒስትር ጃንካርሎ ጆርጌቲ ጋር ውጤታማ ውይይት አድርጓል።
በውይይቱ ጣሊያን የኢትዮጵያን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ ለመደገፍና ከዓለም ባንክ የበጀት ድጋፍ ፕሮግራም ጋር በመተባበር የልማት ፖሊሲዎችን ለማገዝ ስምምነት ላይ ደርሳለች። ይህም ኢትዮጵያ እየተገበረች ላለው የኢኮኖሚ ለውጥ ወሳኝ አቅም እንደሚሆን ተገልጿል።
ጣሊያን የኮይሻ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክትን ለማጠናቀቅና ቀሪውን የፋይናንስ ክፍተት ለመሙላት ያላትን ቁርጠኝነት በድጋሚ ያረጋገጠች ሲሆን፣ የፕሮጀክቱን ፋይናንስ መልሶ ለማደራጀት የተጀመሩ ሥራዎች በጥቂት ወራት ውስጥ እንዲጠናቀቁ መግባባት ተፈጥሯል።
በተጨማሪም በቢሾፍቱ አውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክት ላይ ሊኖር የሚችለውን ትብብር ላይ የመከሩ ሲሆን የጣሊያኑ ሚኒስትር የኢትዮጵያ አየር መንገድን ውጤታማነት አድንቀው፣ በጣሊያን የፋይናንስ ተቋማት አማካኝነት ለአየር መንገዱ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ድጋፍ ለማድረግና የቴክኒክ ውይይቶችን ለመጀመር ተስማምተዋል።
ይህ ስትራቴጂካዊ አጋርነት በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋግረዋል ተብሎ ይጠበቃል።