የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ውስንነት እና የዋጋው መወደድ ለአርሶ አደሩ ግብዓቱን በቀላሉ ለማግኘት አዳጋች አድርጎት እንደቆ ከኢትዮጵያ ሬድዮ ጋር ቆይታ ያደረጉ የክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊዎች ተናግረዋል።
የአፈር ማዳበሪያ ለምርት ዕድገት ወሳኝ ግብዓት እንደሆነ የጠቀሱት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪ እና የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ኡስማን ስሩር ናቸው።
በከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ በሀገር ውስጥ ግንባታው የተጀመረው የዩሪያ ማዳበሪያ ማምረቻ ፋብሪካ ለረጅም ጊዜ የተቸገርንበትን የማዳበሪያ እጥረት እና የዋጋ ውድነት ይፈታል ብለዋል ኃላፊው።
አሁን እየተጠቀምነው ያለው ማዳበሪያ ከውጭ እንደመምጣቱ ይህን በሀገር ውስጥ ማቅረብ መቻል ከውጭ ምንዛሪ ፍለጋ ጀምሮ ያሉ ውስብስብ ውጣ ውረዶችን የሚያስቀር መሆኑን የጠቀሱት አቶ ኡስማን፤ ይህ የኢኮኖሚውን የዕድገት ፍጥነትም የሚጨምር ነው ብለዋል።
በአማራ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኃላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) በበኩላቸው፥ ትልልቅ ፕሮጀክቶችን ጨርሳ ማሳየት የቻለችው ኢትዮጵያ አሁን የጀመረችው የማዳበሪያ ፋብሪካ የምግብ ሉዓላዊነት ማረጋገጫ አንዱ መሣርያ ነው ብለዋል።
የማዳበሪያ ፋብሪካ በሀገር ውስጥ ማቋቋም መቻል ግብዓቱን ለማስገባት እና ለማሰራጨት የነበረውን አስቸጋሪ ሂደት እንደሚቀርፍ ያነሱት ዶ/ር ድረስ፤ በዋጋ ረገድም አርሶ አደሩ ማዳበሪያውን በተመጣጣኝ ዋጋ አንዲያገኝ አስቻይ ሁኔታ ይፈጥራል ብለዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሶማሊ ክልል ግንባታው የተጀመረው የማዳበሪያ ማምረቻ ፋብሪካ በዳንጎቴ ግሩፕ እና በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ በሽርክና የሚገነባ ነው።
ለምርት መጨመር ወሳኝ አስተዋፅዖ የሚያበረክተውን የአፈር ማዳበሪያ በሚፈለገው መጠን በወቅቱ ማግኘት ለኢትዮጵያ አርሶ አደሮች ፈተና ሆኖ ቆይቷል።
በሲሳይ ደበበ
#ebcdotstream #fertlizer #urea