በሄዱበት ሁሉ ይከተላቸዋል። እነርሱም የሰንደቅ ዓላማን ትርጉም በዓለም መድረክ በጉልህ አሳይተዋል፤ ክብሩንም በሚገባ ኖረውታል።
ሀገራቸውን በወከሉባቸው ዓለም አቀፍ መድረኮች ለዚህ ሰንደቅ ዓላማ ብዙ ዋጋ ከፍለዋል። ሰንደቅ ዓላማው ያላቸውን ክብር በንግግር ብቻ ሳይሆን በተግባር ገልጠዋል።
ከልምምድ እስከ ውድድር ወድቀዋል፣ ተነሥተዋል፤ ወጥተዋል፣ ወርደዋል። አሸንፈው በሜዳልያ ፖዲየም ላይ ሲገኙ እንኳን ከዐይናቸው ዕንባ አይጠፋም።
ለአፍሪካውያን አትሌቶች ፈር ቀዳጅ ከሆነው አትሌት አበበ ቢቂላ እስከ ማሞ ወልዴ፤ ከምሩፅ ይፍጠር እስከ ደራርቱ ቱሉ፤ ከኃይሌ ገ/ሥላሴ እስከ ፋጡማ ሮባ፤ ከገዛኸኝ አበራ እስከ ቀነኒሳ በቀለ እና ስለሺ ስህን እንዲሁም ከመሠረት ደፋር እስከ ጥሩነሽ ዲባባ እና ሌሎችም የሀገራቸውን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ አድርገው አውለብልበዋል።
የሚገርመው ብዙዎቹ አድካሚ በሚባሉ ውድድሮች ከተፎካካሪዎቻቸው ጋር ብቻ ሳይሆን ከሕመም ጋር እየታገሉም ጭምር ለሀገር እና ለሰንደቅ ዓላማ የሚከፈለውን ዋጋ ለዓለም ማሳየታቸው ነው።
ኢትዮጵያን ከኦሊምፒክ ጋር ብቻ ሳይሆን ብዙዎች ከሚናፍቁት ነገር ግን ከማያሳኩት የወርቅ ሜዳልያ ጋር ያስተዋወቃት ሰው አትሌት አበበ ቢቂላ የሠራውን ገድል አፍሪካ ብቻ ሳይሆን ዓለም አይዘነጋውም።
ብዙ የአፍሪካ ሀገራት ከቅኝ ግዛት ሙሉ በሙሉ ባልተላቀቁበት በዚያን ዘመን አንድ ኢትዮጵያዊ ለዚያውም ለጥቂቶች ብቻ ትኩረት በሚሰጥበት የኦሊምፒክ መድረክ 42 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነውን ማራቶን በባዶ እግሩ ሮጦ ማሸነፉ ለአውሮፓውያኑ እንግዳ ነገር ነበር።
አበበ ቢቂላ በሮም ጎዳናዎች በዚያ በሚያቃጥል አስፓልት ላይ በባዶ እግሩ እስከ መጨረሻው በፅናት የመቆሙ ምሥጢር ከሰንደቅ ዓላማ ውጭ ምን ሊሆን ይችላል?
ለአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነው የወርቅ ሜዳልያ ከተገኘ በኋላ ወትሮውንም ለዓለም አዲስ ያልሆነው የኢትዮጵያ አርማ አበበ ብቻውን ሮምን በወረረበት ዕለትም ከፍ ብሎ ተውለብልቧል።
ከ18 ዓመት በፊት በጃፓን ኦሳካ በተካሄደው የዓለም አትሌቲከስ ሻምፒዮና በሴቶች 10 ሺህ ሜትር ሩጫ፣ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ ካጋጠማት የሆድ ሕመም ጋር እየታገለች ያሸነፈችበት ከስተትም የሚረሳ አይደለም።
ከፍተኛ የሆነ ሙቀት እና ወበቅ በነበረበት በዚያ ትልቅ መድረክ የሆድ ሕመም ተጨምሮበት ውድድሩን ምን ያህል ፈታኝ እንዳደረገባት መገመት ከባድ አይሆንም።
እጀግ ጠንካራ የሆኑ አትሌቶች በነበሩበት መድረክ ከጠነከረው የሆድ ሕመም ጋር በመታገል አትሌቷ በጽናት የቆመችበት እና እነዚህ ሁሉ ፈተናዎች በሀገር ፊት ሲሆኑ ምንም አለመሆናቸውን አሳይታበታለች።
በሰዓቱ ውድድሩን ካጠናቀቀች በኋላ በሕይወቷ እንዲህ ዓይነት ፈተና ገጥሟት እንደማያውቅ የገለጸችው ጥሩነሽ ዲባባ፣ “ውድድሩን የጨረስኩት ሀገሬ ስለሆነች ነው፤ ሌላ ውድድር ቢሆን አቋርጥ ነበር” በማለት ለሰንደቅ ዓላማ ያላትን ፍቅር እና ክብር በተግባር ያሳየችበት ሲታወስ ይኖራል።
የብዙ ኢትዮጵያውያን አትሌቶችም ታሪክ ይኸው ነው። ማንም በተመቻቸ መንገድ የሀገሩን ክብር ከፍ ያደረገ የለም፤ የመጨረሻዋን መስመር ለማለፍ የመጨረሻ አቅማቸውን ተጠቅመዋል። ለዚህ ደግሞ ውድድሮቹን ደግሞ መመልከትም፣ ማስታወስም በቂ ነው።
በቡዳፔስት ዓለም አትሌቲከስ ሻምፒዮና በተመሳሳይ 10 ሺህ ሜትር የተሳተፈችው አትሌት ጉዳፍ ፀጋይ ጉልበቷ ላይ የገጠማት ጉዳት ከአሸናፊነት አላገዳትም። አይደለም ከሕመም ጋር እየታገሉ ይቅርና በሙሉ ጤና እንኳን ሆኖ ፋታ የማትሰጠው አትሌት ሲፈን ሀሰን ባለችበት ውድድር ጉዳፍ ሕመሟን ችላ የወርቅ ሜዳልያውን የወሰደችበት የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።
በዚሁ መድረክ በሴቶች ማራቶን አትሌት ያለምዘርፍ የኋላው አድካሚውን ውድድር ለመጨረስ በምታደርገው ጥረት ራሷን የሳተችበት ክስተት ሌላ ለሰንደቅ ዓላማ የተከፈለ ዋጋ ሆኖ አልፏል።
አትሌት ቲኪ ገላና በለንደን ኦሊምፒክ ማራቶንን ስታሸነፍ በመውደቅ እና በመነሣት የታጀበ ነበር። የትራክ ንጉሡ አትሌት ኃይሌ ገ/ሥላሴ እና ደራርቱ ቱሉን ጨምሮ በርካታ አትሌቶች በትልልቅ መድረኮች ለመድመቃቸው ምከንያቱ ለሰንደቅ ዓላማ የከፈሉት ዋጋ ነው።
ለዚያም ነው ነፃነት እና አንድነት የሚገለጥባትን ሰንደቅ ዓላማ ሲመለከቱ ዕንባ የሚቀድማቸው እና ሀገራቸው ከፊታቸው የሚሣለው።
በአንተነህ ሲሳይ