Search

እየተጠናከረ የመጣው የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ግንኙነት

ሰኞ ጥቅምት 03, 2018 530

በአውሮፓውያኑ ታኅሳስ 12 ቀን 2024 በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል የተፈረመው የአንካራ ስምምነት የሁለቱን ሀገራት የሁለትዮሽ ግንኙነት በከፍተኛ ሁኔታ አሻሽሏል።
የኢትዮጵያን የቀይ ባሕር መውጫ ጥያቄን ተከትሎ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ግንኙነት እንዲሻክር በሦስተኛ ወገን ጥረት ቢደረግም፣ ከጉርብትና አልፎ የደም ትስስር ያላቸው ሁለቱ ሀገራት ግን ወደ ተሻለው መንገድ መጥተዋል፡፡
በሦስተኛ ወገን በተደረገው ጫና ምክንያት ሶማሊያ የያዘችው አቋም ወደ ትክክለኛ መንገድ የመጣው ከሁለቱም ሀገራት ጋር ጠንካራ ግንኙነት በአላት ቱርክ በተመቻቸው የአንካራ ስምምነት ነው።
ሶማሊያ የኢትዮጵያ የቀይ ባሕር መውጫ ጥያቄ ትክክለኛ በመሆኑ እንደምትቀበለው ሰትገልጽ፣ ኢትዮጵያ የሶማሊያን የግዛት አንድነት በማክበር የባሕር በር ጥያቄዋን ለመቀጠል ተስማምተዋል።
ከዚያ ባለፈ ሁለቱ ሀገራት የቆየውን ታሪካዊ ግንኙነታቸውን በማጠናከር ለቀጣናው ሰላም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማድረግ ተስማምተዋል፡፡ ይህን ተከትሎ የሁለቱ ሀገራት ሙሉ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን እያጠናከሩ በመሪዎች ደረጃም በተደጋጋሚ ተገናኝተው መክረዋል።
የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ ሙሐመድ በተደጋጋሚ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት የሥራ ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሞቃዲሾ የሥራ ጉብኝት አድርገዋል።
መሪዎቹ በሚያወጧቸው የጋራ መግለጫዎችም የደኅንነት ትብብርን ለማጠናከር እና ቀጣናው ላይ ስጋት የደቀነውን ሽብርተኝነት በጋራ ለመዋጋት ተስማምተው ወደ ሥራ ገብተዋል፡፡
የመሠረተ ልማት ትስስርን በማስፋፋት ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቶችን፣ ንግድን እና ኢንቨስትመንትን ማጠናከርም ሁለቱ ሀገራት እየሠሩባቸው ያሉ ጉዳዮች ናቸው።
የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ ሙሐመድ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ለመመረቅ ከተገኙ መሪዎች መካከል አንዱ ሲሆኑ፣ የግድቡን ሪቫን እንዲቆርጡ መጋበዛቸው የግንኙነቱ መሻሻል ማረጋገጫ ነው፡፡
ፕሬዚዳንቱ በቅርቡ ከአል-ዓረቢያ ጋር ባደረጉት ቆይታም በርካታ ኢትዮጵያን የተመለከቱ ጉዳዮችን ያነሱ ሲሆን፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በተመለከተ በሰጡት ሀሳብ ግድቡ ማንንም እንደማይጎዳ አስምረውበታል፡፡
ኢትዮጵያ ረጅም ድንበር የምትጋራቸው የረጅም ጊዜ ጎረቤታቸው እንደሆነች ጠቅሰውም፣ የኢትዮጵያ ልማት ሶማሊያን እንደሚጠቅም አንስተዋል፡፡
የኢትዮጵያ የቀይ ባሕር ጥያቄም ትክክለኛ መሆኑን የጠቀሱት ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ፣ በዚህ ምክንያት ማንም ግጭት ውስጥ መግባት እንደሌለበት ጠቁመዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ትላንትም በኢትዮጵያ የሥራ ጉብኝ በማድረግ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጋር የመከሩ ሲሆን፣ በቀጣናው ሰላምና መረጋጋትን ለማጠናከር ከኢትዮጵያ ጋር እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል፡፡
መሪዎቹ ሁለቱ ሀገራት በኢኮኖሚ፣ ኢንቨስትመንት እና ንግድ ያላቸውን ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር የተስማሙ ሲሆን፣ ጠንካራ የኢኮኖሚ ትብብር በመፍጠር የንግድ ትስስራቸውን የሚያሳልጡ የመሰረተ ልማት መስመሮችን ለማስፋት እና የጋራ ብልፅግናቸውን ለማረጋገጥ ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።
 
በለሚ ታደሰ