የኮሪደር ልማት ጅማሮው የአሶሳ ከተማን ገፅታ በእጅጉ ቀይሮታል። ቆሻሻ መጣያ የነበሩ ቦታዎች አሁን ላይ የበርካቶች መዝናኛ ስፍራ ሆነዋል።
በከተማዋ የተከናወነው የኮሪደር ልማት ተጠናክሮ መቀጠሉንም የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ መሀመድ አልማሂ ገልጸዋል።
አሶሳ ከተማን ውብና ለነዋሪዎቿ ምቹ ለማድረግ የተከናወኑ ሥራዎች የተሻለ ውጤት ተገኝቶባቸዋል ያሉት አቶ መሀመድ አልማሂ ፤ በመጀመሪያ ዙር የኮሪደር ልማት 9.6 ኪሎ ሜትር መሠራቱን አስታውሰዋል።
በሁለተኛው ዙር ደግሞ በከተማዋ በተመረጡ ቦታዎች ላይ የኮሪደር ልማት ሥራው እንደሚከናወን አስታውቀው፤ ኅብረተሰቡ ለልማቱ የሚያደርገውን ድጋፍ እና ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
ለኢቢሲ ሃሳባቸውን የሰጡ የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎችም ለከተማዋ የኮሪደር ልማት ሥራ አስፈላጊውን ትብብር እያደረጉ መሆኑን ገልፀው፤ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም ተናግረዋል።
የኮሪደር ልማት ሥራው በክልሉ በሚገኙ ዞኖች እና የተለያዩ ከተሞች ላይም ተግባራዊ እንደሚደረግ ተገልጿል።
በጀማል አህመድ