ኢትዮጵያ የግብርናውን ዘርፍ ምርታማነት በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የሚያስችላትን ሥራ እያከናወነች ስለመሆኗ ይነሣል።
ይህም የገጠሩን የኢኮኖሚ አቅም በፍጥነት እና በፈጠራ በማንቀሳቀስ አርሶ አደሩን ማዕከል ያደረገ ልማትን ለማረጋገጥ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመደመር መንግሥት መጽሐፍ ላይ ጠቅሰውታል።
በዚሁ እሳቤ መሠረት ባለፉት ዓመታት በስንዴ ልማት ዘርፍ ላይ የተሰጠው ትኩረት ውጤታማ ሆኗል።
በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ዓመታዊ የስንዴ ምርት 340 ሚሊዮን ኩንታል ስለመድረሱም የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል። ከ8 ዓመታት በፊት ግን ከ50 ሚሊዮን ኩንታል በታች ነበር።
የምርቱ ማደግ ሀገሪቱ ከውጭ ታስገባው የነበረውን ስንዴ በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት ከማስቻሉም በላይ ወደ ውጭ ለመላክም አስችሏል ነው የተባለው።
የግብርና ተመራማሪው ፕሮፌሰር ፍሬው መክብብ በጉዳዩ ላይ ከኢትዮጵያ ሬዲዮ ‘የኢትዮጵያ ድምፅ’ የዜና ሰዓት ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ የመንግሥት ድጋፍ እና የአመራር ቁርጠንኝነት መጠናከር እንዲሁም የመስኖ ልማት መስፋት በስንዴ ምርት ላይ ለተገኘው ውጤት ሚናቸው የጎላ ነው ብለዋል።
የአርሶ አደሮች ታታሪነት፤ የክላስተር አመራረት መጨመር እና የምርምር ሥራዎችም በስንዴ ምርት ዕድገት ላይ ከፍ ያለ አስተዋፅኦ እያደረጉ ነው ያሉት ፕሮፌሰር ፍሬው፣ በዚህም አሁን ላይ ኢትዮጵያ በስንዴ ምርት ሉዓላዊት ሀገር መሆን ችላለች ሲሉ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በስንዴ ምርት ላይ ያስመዘገበችው ውጤት በአፍሪካ የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ በኩል ሞዴል ተደርጋ ልትወሰድ እንደምትችል የሚያሳይ መሆኑንም ተመራማሪው ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ ለግብርና የተመቸች ሀገር ናት ያሉት ፕሮፌሰር ፍሬው፣ ሀገሪቱን የአፍሪካ የዳቦ ቅርጫት ማድረግ እንደሚቻልም ተናግረዋል።
ይህ እንዲሳካ ግን በስንዴ ላይ የተገኘውን ተሞክሮ በሌሎች ሰብሎች ላይ ማሳየት እንዲሁም ሀገሪቱ ያላትን ከፍተኛ በመስኖ የመልማት አቅም መጠቀም ያስፈልጋል ብለዋል።
የወደፊቱ የኢትዮጵያ የግብርና ምርት የሚወሰነው በመስኖ ነው የሚሉት ተመራማሪው፣ ለዚህም ባለሃብቱ ያለውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም መሥራት እንዳለበት አስገንዝበዋል።
ይህ ሲሆን የገጠሩ ማኅበረሰብ እና ግብርናው በሚፈለገው ልክ ይለወጣል ባይ ናቸው። አምራቹን እንዲያመርት ከመደገፍ ባሻገር በግብይቱ ላይ በቀጥታ በማሳተፍ የምርቶች ዋጋ እንዲረጋጋ ማድረግ ይገባልም ብለዋል።
በኢትዮጵያ የግብርና ምርት ዕድገት ላይ የምርምር ሥራዎች ሚናቸው የጎላ ነው መሆኑን ጠቅሰው፣ እስካሁን ከ1 ሺህ 600 በላይ የሰብል ዝርያዎች ተሻሽለው ተለቅቀዋል ሲሉ ገልጸዋል።
ይሁንና እነዚህን የምርምር ውጤቶች በሙሉ ወደ አርሶ አደሩ ማድረስ ላይ ውስንነት መኖሩን በመጠቆም፣ በቀጣይ ይህን ማሻሻል እንደሚያስፈልግ እና ዘመናዊ የባዮቴክኖሎጂ ምርምሮችን ማሳደግም የግድ እንደሚሆን አስገንዝበዋል።
በብርሃኑ አለሙ
#ethiopianradio #EBC #ebcdotstream #Ethiopia #wheat #foodsovereignty