በትናንትናው ዕለት የተመረቀው አዲስ ሲኒማ ኮምፕሌክስ መንግሥት ለኪነጥበብ ማንሰራራት ያለውን ፍላጎት ያሳየበት ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ፡፡
ዘመናዊ እና በአይነቱ ልዩ የሆነው አዲስ ሲኒማ ኮምፕሌክስ ትውልድ ተሻጋሪ ስራ ነው ብለዋል፡፡
ለኪነ ጥበቡ ትልቅ ቦታ በመስጠትም በከፍተኛ ወጪ እንደተገነባም ነው ያነሱት፡፡
የኢትዮጵያን የፊልም ኢንዱስትሪ በዓለም አደባባይ ከፍ ለማድረግና የኢትዮጵያ ባህል እና እሴቶች ለማስተዋወቅ አቅም እንዳለው ጠቅሰዋል፡፡
ነባር ሲኒማ ቤቶች ዘመኑን የዋጁ ባለመሆናቸው ለአገልግሎት ምቹ እንዳልነበሩ ያነሱት ከንቲባዋ፤ ምቹ ያልሆኑ ሲኒማ እና ትያትር ቤቶችን በማደስ ለአገልግሎት ክፍት መደረጋቸውን ገልፀዋል፡፡
በለውጡ መንግሥት 5 ሲኒማ ቤቶችም ስለመገንባታቸው አስታውሰው፤ አዲስ ሲኒማ ኮምፕሌክስ 15 ወለል ያለው እና በውስጡ በርካታ አገልግሎቶችን ያካተተ ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡
ኪነጥበብ አንድነትን እና ብልጽግናን የሚያረጋግጥ መሳሪያ በመሆኑ በዘርፉ ያሉ ባለሞያዎች ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡
በሜሮን ንብረት
#EBC #ebcdotstream #AddisAbaba #addiscinema