በአማራ ክልል የፅንፈኛው ኃይል በሚንቀሳቀስባቸው አካባቢዎች ያሉ የመማሪያ ክፍሎች ተማሪዎችን ካስተናገዱ ሰንብተዋል።
ምክንያቱ ድግሞ የታጠቁት ፅንፈኛ ኃይሎች መምህራን እና ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዳይሄዱ ክልከላ በማድረጋቸው ነው።
ትምህርት ለአንድ ሀገር ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ዕድገት እንዲሁም የፖለቲካ መረጋጋት ወሳኝ ጉዳይ ነው። እንደ ኢትዮጵያ ውስብስብ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ሁኔታ ውስጥ ላለ ሀገር ደግሞ ተምሮ ለውጥ የሚያመጣ ትውልድ ያስፈልጋል።
የየትኛውም ሀገር የዕድገት እና ብልፅግና መሠረት ትምህርት በመሆኑ፣ የሐሳብ ነፃነት ያለው እና ለሀገሩ የሚበጀውን መንገድ ማመላከት የሚችል ትውልድ የሚፈራው በትምህርት ነው።
ለዚህም ነው ትምህርት ከማንኛውም የፖለቲካ አስተሳሰብ ነፃ መሆን አለበት የሚባለው። ሥልጣን ላይ ያለውም ሆነ ለሥልጣን የሚታገለው ወገን ነገን የሚያስብ ከሆነ ትምህርትን ከተፅዕኖ ነፃ ማድረግ አለበት።
በአንዳንድ የሀገራችን አካባቢዎች ግን ሕፃናት በነፃ አዕምሮ እንዳይማሩ ተፈርዶባቸዋል። ሕፃናት እስከ ሦስት ተከታታይ ዓመታት ወደ ትምህርት ቤት እንዳይሄዱ ከተከለከለባቸው ክልሎች አንዱ አማራ ክልል ነው።
ለሕዝብ እታገላለሁ የሚለው ፅንፈኛ ቡድን በክልሉ በጫረው ግጭት ምክንያት የትምህርት ዘርፉ ከፍተኛ ተግዳሮት ገጥሞታል። ግጭቱ የትምህርት ቤት መዘጋት፣ የተማሪ ምዝገባ መቀነስ፣ ከፍተኛ መፈናቀል እና በትምህርት መሠረተ ልማት ላይ ወድመትን አስከትሏል።
በዚህም ምክንያት ከ4.1 ሚሊዮን በላይ ሕፃናት ከትምህርት ገበታ ውጪ መሆናቸው እና ትምህርት ከጀመሩ በኋላም ጫና እየተደረገባቸው ለማቋረጥ የሚገደዱ ተጨማሪ ሕፃናት እንደሚኖሩም ተጠቅሷል።
የክልሉ ትምህርት ቢሮ በ2018 የትምህርት ዘመን 7.4 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችን ለመመዝገብ አቅዶ የተንቀሳቀሰ ቢሆንም፣ እስካሁን ተመዝግበው ትምህርት የጀመሩት 3.4 ሚሊዮን ብቻ ናቸው። በተለይ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ያለው ምዝገባ በጣም ዝቅተኛ እንደሆነ ነው ቢሮው የገለጸው።
የቢሮው መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በክልሉ ከሚገኙ 11 ሺህ 69 ትምህርት ቤቶች መካከል 2 ሺህ 445 ትምህርት ቤቶች በሰላም እጦቱ ምክንያት ተዘግተዋል፤ በርካታ ትምህርት ቤቶችም በፅንፈኞቹ ወድመዋል፤ ተዘርፈዋል።
መምህራን እና የትምህርት ሠራተኞች በታጣቂዎች የመታገት፣ ማስፈራሪያ እና ጥቃት እየደረሰባቸው በመሆኑ እንደልብ ማስተማር እንዳልተቻለ በተለያዩ ጊዜያት የወጡ ሪፖርቶች አመላክተዋል።
በገጠር እና ግጭት ባሉባቸው አካባቢዎች ያሉ ሕፃናት የመሃይምነት አዋጅ ታውጆባቸው ወደ ትምህርት ቤት ከሄዱ ዓመታት አልፏቸዋል።
የክልሉ የትምህርት ቢሮ ከአጋሮቹ ጋር በመሆን እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ በርካታ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታ ለመመለስ ጥረቶችን እያደረገ ይገኛል።
በዚህ ዓመት የክልሉ ትምህርት ቢሮ ከዚህ ቀደም የደረሱ የመማር ማስተማር ኪሳራዎችን ለማካካስ እና ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዲመለሱ ለማበረታታት የተለያዩ ጥረቶችን አድርጎ ካለፉት ዓመታት የተሻለ ውጤት ቢገኝም አሁንም የሚጠበቀው ውጤት እየመጣ አይደለም።
ልጆቹን ወደ ትምህርት ቤት መላክ ዳገት የሆነበት የክልሉ ማኅበረሰብ በዚህ ጉዳይ ላይ ምሬቱን በከፍተኛ ሁኔታ እያሰማ ይገኛል።
አቶ ተመስገን አበበ (ስማቸው የተቀየረ) የወላጅ ተማሪ መማክርት አባል ናቸው። ሕፃናት ለሰሦስተኛ ዓመት ከትምህርት ውጭ እየሆኑ መሆናቸውን የጠቀሱት አቶ ተመስገን፣ የዘንድሮ ምዝገባ ከሌላው ጊዜ ሻል ያለ ቢሆንም ከከተሞች ርቀው በሚገኙ አካባቢዎች ላይ ተመሳሳይ ችግር እንደቀጠለ ተናግረዋል። በትምህርት ማጣትም ሆነ በሌላው ማኅበራዊ ምስቅልቅል ግንባር ቀደም ተጠቂ የሆነው የድሃ ልጅ እንደሆነ የጠቀሱት አቶ ተመስገን፣ "ፖለቲከኛ ነኝ የሚለው አካል እውነት ለሕዝብ የሚያስብ ከሆነ የነገውን ትውልድ ተስፋ መግደል የለበትም" በማለት ድርጊቱን ኮንነዋል። ሕፃናት በማይመለከታቸው ጉዳይ ተስፋቸው እንዲቀጭጭ እየተደረጉ እንደሆነ ጠቅሰው፣ "ሰላም በማስከበር ጉዳይ የመንግሥት ሆደ ሰፊነት ሕዝቡ ምን እስከሚሆን መጠበቅ ነው?" ብለው ጠይቀዋል።
አቶ ያየህ መላኩ (ስማቸው የተቀየረ) የደብረ ኤልያስ ወረዳ ነዋሪ እና ርዕሰ መምህር ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት በወረዳው ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት ከሄዱ ሦስት ዓመት ሆኗቸዋል። ዘንድሮ በተደረገው እንቅስቃሴ ለውጥ መታየቱን የጠቀሱት አቶ ያየህ፣ ፅንፈኞቹ መምህራንን እየደወሉ እያስፈራሩ፣ በየቤተክርስቲያኑም እየሄዱ ወላጆች ልጆችን ወደ ትምህርት ቤት እንዳይልኩ ያስፈራራሉ ብለዋል። ልጆች ለትምህርት ያላቸው ጉጉት እጅግ አንጀት የሚበላ እንደሆነ የጠቀሱት አቶ ያየህ፣ ኅብረተሰቡም ግራ ተጋብቶ ዝም እንዳለ ጠቅሰዋል። በዚህ ምክንያት በርካታ ሕፃናት ተስፋ እየቆረጡ ለድባቴ እየተዳረጉ እንዲሁም ሴት ልጆች ደግሞ ያለ ዕድሜያቸው ለጋብቻ እየተዳረጉ እንደሆነ ጠቁመዋል።
አቶ መክት ያለው (ስማቸው የተቀየረ) የቡሬ ወረዳ ነዋሪ ሲሆኑ ፅንፈኛው ቡድን "እኛ ካልፈቀድን ትምህርት ቤት መሄድ የለባችሁም" በማለት የሕፃናትን ብርሃን እየጋረደ ነው ብለዋል። "ለአማራ እታገላለሁ የሚለው ቡድን ትውልድ እየገደለ ማንን ሊመራ ነው?" ብለው የሚጠይቁት አቶ መክት፣ እውነት ለሕዝቡ የሚያስብ ከሆነ ለትውልድ ድንቁርናን ማውረስ የለበትም ብለዋል።
ታጣቂዎቹ እያደረሱ ባለው ጥፋት በርካታ ሕፃናት ተስፋቸው እየጨለመ መሆኑን የገለጹት ደግሞ አቶ አበጀ ቻላቸው (ስማቸው የተቀየረ) ናቸው።
እርሳቸው ባሉበት ወረዳ መምህራንን ሰብስቦ እስከ መረሸን የደረሰ አስከፊ እርምጃ በፅንፈኞቹ መወሰዱን ጠቅሰው፣ በርካታ መምህራን ይህን ችግር በመፍራት ለማስተማር እየተሳቀቁ መሆኑን ተናግረዋል።
በምዝገባ ረገድ በዚህ ዓመት ካለፉት ዓመታት በጥቂቱም ቢሆን የተሻለ ሁኔታ መኖሩን ጠቁመው፣ አሁንም ቢሆን ዛሬ ታይተው ነገ የሚጠፉ ሰዎች ስላሉ የትምህርቱ ጉዳይ ሙሉ በሙሉ እንደ ልብ እንዳልሆነ ገልጸዋል።