የብልፅግና ፓርቲ የ2018 በጀት ዓመት 1ኛ ሩብ ዓመት የፓርቲ ሥራዎች አፈጻጸም ግምገማ መድረክ መካሄድ ጀመረ።
ከዛሬ ጀምሮ ለሁለት ተከታታይ ቀናት በፓርቲው ዋናው ጽ/ቤት እየተካሄደ በሚገኘው መድረክ የብልፅግና ፓርቲ ም/ፕሬዚዳንትና የዋና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ፣ የብልፅግና ፓርቲ ዋና ጽ/ቤት የዘርፍ ኃላፊዎች፣ የሁሉም ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊዎች እና ሌሎች የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።

የሩብ ዓመቱን የፓርቲ ሥራዎች አፈጻጸም ግምገማ መድረክ በንግግር የከፈቱት አቶ አደም ፋራህ፤ ፓርቲውን ለስኬት ያበቁትን አንኳር ነጥቦችን አብራርተዋል።
ፓርቲው በሁሉም ዘርፎችና መስኮች ስኬታማ ጉዞ እያደረገ ይገኛል ሲሉም ተናግረዋል።
ለኢትዮጵያና ለፓርቲያችን በሚመጥን መንገድ በመደመር እሳቤ ሁሉንም አቅሞች ለመጠቀም ጥረት በመደረጉ፤ በፕራግማቲክ (ገቢር ነበብ) እይታ በየአካባቢው ያለውን ተግባራዊ እውነታ መሰረት በመደረጉ፤ በፍጥነትና በፈጠራ መርህ በመሰራቱና ፈተናን ወደ ዕድል የመቀየር መርህ መከተል በመቻሉ ፓርቲው ዘርፈ ብዙ ስኬቶችንና ድሎችን አስመዝግቧል ብለዋል።
በመድረኩ በፓርቲውና በሕዝብ ንቅናቄ የተሰሩ ሥራዎች በጥልቀት የሚገመገሙ ሲሆን፤ በሁሉም መስኮች የተመዘገቡ ስኬቶችን ማስቀጠል እና ጉድለቶችን ለማረም የጋራ መግባባት ይፈጠራል ተብሎ ይጠበቃል።
በዮሐንስ ፈንታሁን