የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ከክልሉ ከተለያዩ ዞኖችና ከተማ አስተዳደሮች የትምህርት አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ጋር የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት የእቅድ አፈጻጸም የግምገማ መድረክ በባህር ዳር ከተማ እያካሄደ ነው።
በክልሉ በዘንድሮው የትምህርት ዘመን 7.4 ሚልየን ተማሪዎችን መዝግቦ ለማስተማር ከታቀደው ውስጥ እስካሁን የተመዘገቡት 3.8 ሚልየን ተማሪዎች ብቻ መሆናቸው ተገልጿል።
በመድረኩ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሙሉነሽ ደሴ (ዶ/ር)፤ በፀጥታ ችግሮች የተነሳ በአለፉት ዓመታት በትምህርት ዘርፉ ላይ ስለደረሰው ስብራት አብራርተዋል።
በዚህም የተነሳ በርካታ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ ሆነው መቆየታቸውን አንስተዋል።
በዘንድሮው የትምህርት ዘመንም ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ ከማድረግ አኳያ ከባለፉት ዓመታት አንፃር ሲነፃፀር የተሻለ ቢሆንም፣ አሁንም በቅንጅት መስራትን ይጠይቃል ብለዋል።
የፖለቲካ ልዩነቶች ተፈጥሯዊ በመሆናቸው ሊፈጠሩ ይችላሉ ያሉት ቢሮ ኃላፊዋ ፤ ትምህርትን ከፖለቲካ አጀንዳነት ማውጣት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በመሆኑም ክልሉ በእውቀት የተካነ ትውልድ እንዳያጣ በመሆኑ፤ ነገን አስቦ ተማሪዎች ወደትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
ለትምህርት ዘርፉ ውጤታማነት ባለድርሻ አካላትን ጨምሮ ሁሉም ጥረቱን አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አመላክተዋል።
በሳሙኤል ወርቃየሁ