Search

በአፋር ክልል የመልሶ ማቋቋም ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል - ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ

ረቡዕ ጥቅምት 12, 2018 40

የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ በተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አደጋዎች ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች የተለያዩ የትምህርት፣ የጤና እና የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶችን አስመርቀዋል።
በክልሉ በሚገኙ ሲፍራ፣ አዳዓርና ኡዋ ወረዳዎች የተመረቁት ፕሮጀክቶች ፤ በኅብረተሰቡ ላይ የነበረውን ተደራራቢ ጫና ለማቃለል ያስችላሉ ተብሏል።
በአጠቃላይ አራት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ አንድ ልዩ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ አምስት የጤና ኬላዎች እና ሦስት የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶች በዓለም ባንክና በጣሊያን መንግሥት ድጋፍ ተሠርተው ተመርቀዋል።
 
የአርብቶ አደሩን ማኅበረሰብ በአንድ አካባቢ የእንስሳት መኖ፣ የመጠጥ ውኃ እና ሌሎች አገልግሎቶችን እንዲያገን በሶላር የሚሰሩ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ወደሥራ መግባታቸውንም ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ ገልፀዋል።
በክልሉ መልሶ መቋቋም ፅ/ቤት አማካኝነት በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ላይ በርካታ መሠረተ ልማት ሥራዎች እየተሰሩ እንደሚገኝም ተጠቁሟል።
በቀጣይ በሌሎች የክልሉ አካባቢዎች መሠል የትምህርት፣ የጤና እና የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶች ተመርቀው ለኅብረተሰቡ አገልግሎት እንደሚሰጡ ተገልጿል።
 
በሁሴን መሀመድ