የተፈጥሮ ጋዝ ከትራንስፖርት እና ከማዳበሪያ ምርት ባለፈ ዘርፈ ብዙ ጥቅም አለው ሲል የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን ገለፀ፡፡
ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ፈሳሽ ጋዝ ማምረት መጀመሯን ተከትሎ ዘርፉን ለማነቃቃት ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ የሆኑት መንግሥቱ ከተማ (ፕ/ር) ከኢቲቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ የተፈጥሮ ጋዝ ከሌሎች ነዳጆች ጋር ሲነጻፀር በዋጋም ሆነ ከባቢ አየርን ከመበከል አንጻርም ዝቅ ያለ እንደሆነ ነው የገለጹት፡፡
የተፈጥሮ ጋዝ ከትራንስፖርት እና ከማዳበሪያ ምርት ባለፈ ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዳለው አንስተው፤ ለአብነትም ለኢንደስትሪዎች፣ ለምግብ ማብሰያ፣ ለሴንቴቲክ ጎማ እና ለሌሎች ዘርፎች እንደሚያገለግል ተናግረዋል፡፡
የተፈጥሮ ጋዝ ሀብት ያላቸው ሀገራት የራሳቸውን ኢኮኖሚ ከመደገፍ ባለፈ በዓለም አቀፍ ግንኙነት ላይ ተፅዕኖ የመፍጠር ኃይላቸው የጎለበተ መሆኑንም አክለዋል፡፡
የተፈጥሮ ጋዝ የሰው ልጅን አናኗር እና ኢንዱስትሪዎችን በመደገፍ ለምጣኔ ሀብት እድገት ወሳኝ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
የተፈጥሮ ጋዝ ፕሮጀክት ግንባታ ኢትዮጵያ የምትከተለውን የአረንጎዴ ኢኮኖሚ ልማት በመደገፍ ትልቅ አበርክቶ እንደሚኖረውም ተመላክቷል።
በሜሮን ንብረት
#ebc #ebcdotstream #Ethiopia #naturalgas