የዓለም ባንክ የኢትዮጵያን የልማት አጀንዳ ለማሳካት ከፍተኛ ትብብር እያደረገ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ ገለጹ።
ሚኒትሩ የቅድመ-ልማት ፕሮጀክቶች፣ በመካሄድ ላይ ያሉ የሪፎርም ሥራዎች እና አዳዲስ የፋይናንሲንግ ዘዴዎች ላይ ያለውን ትብብር ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ከዓለም ባንክ የኦፕሬሽን ጉዳዮች ማኔጂንግ ዳይሬክተር አና ቢየርደ ጋር ተወያይተዋል።
የዓለም ባንክ የኢትዮጵያን ታላቅ የልማት አጀንዳ ለማሳካት ያለውን ከፍተኛ ሚና ዕውቅና በመስጠት፤ እየተደረገ ለሚገኘው ከፍተኛ የቴክኒክ እና የፋይናንስ ድጋፍ አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በማዘመን፣ ምርታማነትን በማሳደግ፣ አዳዲስ የዕድገት መንገዶችን በመፍጠር እና የግሉ ዘርፍ ተሳትፎን በማጎልበት የሥራ ዕድል ለመፍጠር እና በመላ ሀገሪቱ የኑሮ ደረጃን ለማሻሻል የባንኩ ድጋፍ ያለውን አስተዋፅዖ አመላክተዋል።
የዓለም ባንክ ከኢትዮጵያ ጋር ባለው የረጅም ጊዜ አጋርነት ለሀገሪቱ ዋና ዋና የልማት ዘርፎች ከ15 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚገመት ድጋፍን ማድረጉን ጠቅሰው ምስጋና አቅርበዋል።
የሥራ ዕድል ፈጠራን፣ ዘላቂ መሠረተ ልማቶችን እና የሰው ኃይል ካፒታል ልማትን ለማስቀጠል የባንኩ ቀጣይ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ሚኒስትሩ አጽንኦት ሰጥተው ገልጸዋል።
ዋና ዳይሬክተሯ አና ቢየርደ በበኩላቸው፥ የኢትዮጵያ መንግሥት ባካሄደው ሪፎርም ምክንያት ጉልህ ዕድገት መመዝገቡን እና የዋጋ ንረት በከፍተኛ ሁኔታ ማሽቆልቆሉን ጠቅሰዋል።
የወጪ ንግድ ማደግ፣ የተሻሻለ የሀገር ውስጥ ገቢ አሰባሰብ እና የፊስካል ማገገም እንዲሁም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተፈጠረ ያለውን ምቹ የንግድ ከባቢ በማንሳት አድናቆታቸውን ገለጸዋል።
ዋና ዋና የሪፎርም እርምጃዎችን በመተግበር ረገድም መንግሥት የጀመረውን ጠንካራ እንቅስቃሴ አጠናክሮ እንዲቀጥል እንደሚያበረታቱም ተናግረዋል።