በጉባ የተበሰሩት ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ኢትዮጵያን ከኢኮኖሚ ስብራት በማውጣት ወደ ሁለንተናዊ ብልጽግና የሚያሸጋግሩ ናቸው ሲሉ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጳጉሜን 4 ቀን 2017 ዓ.ም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በመረቁበት ወቅት፣ በቀጣይ ጥቂት ዓመታት በ30 ቢሊዮን ዶላር የሚገነቡ ትላልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን አብስረዋል፡፡
የኒኩለር ኃይል ማመንጫ፣ የማዳበሪያ ፋብሪካ፣ የቢሾፍቱ አየር መንገድ፣ የተፈጥሮ ጋዝ ማምረቻ፣ የነዳጅ ማጣሪያና የቤቶች ልማት በወቅቱ ከተበሰሩ ፕሮጀክቶች መካከል በዋናነት ይገኙበታል፡፡
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ እውነቱ አለነ፤ የጉባ ብስራቶች በመላው ኢትዮጵያውያን ርብርብ እውን የሆነው የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ይዟቸው የመጣ ትሩፋቶች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ግድቡ ኢንዱስትሪዎችን፣ ቴክኖሎጂዎችንና ኢንቨስትመንቶችን ለማስፋፋት ከፍተኛ አቅም እንደሚሆን ጠቅሰው፤ በኃይል አቅርቦት ዙሪያ ይነሱ የነበሩ ጥያቄዎችን የሚፈታ እና ሌሎች ፕሮጀክቶችን ወደ መገንባት እንድንሸጋገር ያደረገ ነው ብለዋል፡፡
ከግዙፍ ፕሮጀክቶች አንዱ የሆነው የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ የማዳበሪያ ምርትን በሀገር ውስጥ በመተካት የውጭ ምንዛሬን ለማዳንና የማዳበሪያ ፍላጎትን ለመሙላት ሁነኛ መፍትሄ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
የቢሾፍቱ አየር መንገድ ፕሮጀክትም አፍሪካን የበለጠ እርስ በእርስ ከማስተሳሰር ባሻገር የአየር መንገዱን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት እንደሚያሳድገው አመላክተዋል፡፡
በምክር ቤቱ የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አራሬ ሞሲሳ በበኩላቸው፤ በጉባ የተበሰሩ የልማት ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና በተግባር የሚያረጋግጡ ናቸው ብለዋል፡፡
በምክር ቤቱ የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል ሞጋ አባቡልጉ፤ ይፋ የተደረጉት ግዙፍ ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን የኃይል አማራጮችና የልማት ግቦች የሚያሰፉ ናቸው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በመሆኑም ፕሮጀክቶቹ በተያዘላቸው ጊዜ እና ወጪ ተጠናቀው ለህዝብ አገልግሎት እንዲበቁ ምክር ቤቱ ሕጎችን በማውጣትና የፓርላማ ዲፕሎማሲዎችን በማሳደግ የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ ተናግረዋል፡፡