Search

ሪፎርሙ ሙሉ ውጤት የሚያሳይበት ዓመት በመሆኑ በ2018 የላቀ ዕድገት ይመዘገባል - ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)

ሓሙስ ጥቅምት 13, 2018 26

የኢትዮጵያ የተሟላ የኢኮኖሚ ሪፎርም ሙሉ ውጤት የሚያሳይበት ዓመት በመሆኑ በ2018 ዓ.ም በጠቅላላው የላቀ ዕድገት እንደሚመዘገብ ይጠበቃል ሲሉ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
እያደገ ያለው የወጪ ንግድ እና በዲጂታል ዘርፍ ታግዞ እየተሻሻለ የመጣው የአገልግሎት ዘርፍ መንግሥት ያሰበውን ጥራት ያለው ኢኮኖሚ ግንባታ እያሳኩት መሆናቸውን ሚኒስትሯ ጠቁመዋል።
በዚህም ምክንያት በዓመቱ መጨረሻ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በ10.2 በመቶ እንደሚያድግ መተንበዩን ነው ሚኒስትሯ የጠቆሙት፡፡
የተተነበየው ዕድገት መነሻ የ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸም መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትሯ፣ ከባለፈው ዓመት ስኬታማ አፈጻጸም በመነሳት በየዘርፉ የታዩ ለውጦች እና ተጨማሪ ሥራዎች የዚህ ዓመት ዕቅዱ እንደሚሳካ የሚጠቁሙ ናቸው ብለዋል።
የተጀመሩ እና ቀድመው የተተገበሩ ሪፎርሞች ሙሉ ውጤት የሚታይበት ዓመት እንደሚሆን አመላካች መሆናቸውን ጠቁመው፤ ለዕድገቱ እውን መሆን አጋዥ ይሆናሉ ሲሉም አስረድተዋል።
የንግድ፣ ኢንቨስትመንት፣ እንዲሁም የአገልግሎት ዘርፉን የሚያሻሽለው የዲጂታላይዜሽን ትግበራም ሌላው ለዕቅዱ መሳካት የሚረዱ ዘርፎች መሆናቸውንም ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) አስታውቀዋል።
በተለይ "መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት" ዜጎች ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ በኢኮኖሚው ውስጥ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደሚሆን ገልጸዋል።
 
በለሚ ታደሰ