Search

የግብርና ሪፎርሙ በተሟላ ሁኔታ ሥራ ላይ መዋል በዘርፉ የታሰበውን እድገት ለማስመዝገብ ያስችላል፡- ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)

ዓርብ ጥቅምት 14, 2018 45

የግብርና ሪፎርሙ በተሟላ ሁኔታ ሥራ ላይ መዋል እና ውጤቱ የሚታይበት ዓመት መሆኑ ዘርፉ የታሰበውን ዕድገት እንዲያስመዘግብ የሚያስችል ነው ሲሉ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
የግብርናው ዘርፍ በ2018 ዓ.ም ማጠናቀቂያ የ7.8 በመቶ ዕድገት እንደሚያስመዘግብ ትንበያ መቀመጡን ሚኒስትሯ ጠቁመዋል፡፡
የሚታረስ መሬት በ3.1 በመቶ እንደሚያድግ የጠቀሱት ሚኒስትሯ፤ የመስኖ፣ ሜካናይዜሽን እና ኮሜርሺያላይዜሽን ሥራዎች መስፋፋት ለዘርፉ ዕድገት አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ ነው የተናገሩት፡፡
የሥጋ እና ሥጋ ውጤቶች መዳረሻ ሀገራት እየጨመሩ መምጣታቸው እንዲሁም የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅን ተከትሎ የሚያድገው የዓሣ ምርት ለግብርና ዕድገቱ መሳካት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ አመላክተዋል፡፡
ከኩታገጠም እርሻ መስፋፋት ጋር ተያይዞ አርሶ አደሩ ውኃውን ከእርሻው ጋር የሚያገናኝባቸው በርካታ የውኃ ፓምፖች የሚሰራጩ መሆናቸው፣ የግብርና ምርታማነት እንደሚጨምሩ ገልጸዋል፡፡
የበጀት ዓመቱ የሦስት ወራት አፈፃፀም ሲታይ የቡና ምርት ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ19 በመቶ ብልጫ እንዳለው አመላክተዋል፡፡
ዘንድሮ በቡና ልማት የተሸፈነው 1.28 ሚሊዮን ሔክታር መሆኑን ሚኒስትሯ ገልጸው፤ ከዚህም ባለፉት 100 ቀናት 7 ሚሊዮን ኩንታል የሚጠጋ የቡና ምርት ተሰብስቧል ነው ያሉት።
በግብርና ውስጥ እየተካሄደ ባለው መዋቅራዊ ሽግግር ምክንያት የሰብል ምርት ስብጥር እያደገ መምጣቱን ጠቅሰው፣ ገበያ መር ሰብሎች እና የሥጋ ውጤቶች ላይ ከፍተኛ ለውጥ እየመጣ መሆኑን ነው ሚኒስትሯ የጠቆሙት፡፡
በለሚ ታደሰ