የኮሪደር ልማት የአዲስ አበባን ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን ገፅታ እየቀየረ መሆኑን የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት እና በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል ኃላፊ አደም ፍራህ ገለፁ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ጋር በመሆን የተጠናቀቀውን የሳር ቤት-ጀርመን አደባባይ-ጋርመንት እና ፉሪ አካባቢ የኮሪደር ልማት ሥራን ጎብኝተዋል።
የኮሪደር ልማቱ እስከ አሁን ከተሰሩት በርዝመቱም ሆነ በሚሸፍነው ስፋት ትልቅ መሆኑን አቶ አደም ፋራህ ጠቁመዋል።

ከኮሪደር ልማት ጋር ተያይዞ የአረንጓዴ ልማት፣ የስፖርት ማዘውተሪያዎች፣ የሕዝብ መፀዳጃ ቤቶች፣ የንግድ ሱቆች መገንባታቸውንም ገልፀዋል። ከእያንዳንዱ የኮሪደር ልማት ትምህርት እየተወሰደ የማሻሻያ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑንም ተናግረዋል።
ሥራው በአጭር ጊዜ ውስጥ ከተማን መቀየር እንደሚቻል ያመላከተ መሆኑንም ገልፀዋል። ይህም የአመራሩን ብቃትና ቁርጠኝነት፣ የባለሙያውን ትጋት እና የኅብረተሰቡን ድጋፍ ያሳየ መሆኑን ጠቁመዋል።
የኮሪደር ልማት ገፅታን ከመቀየር ባለፈ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑንም አስረድተዋል።
የኮሪደር ልማቱ እንደ ሀገር በተለያዩ ከተሞች እየተስፋፋ መሆኑን ጠቁመው፤ ለሌሎች ታዳጊ አፍሪካ ሀገራትም ምሳሌ መሆን የሚችል ሥራ እንደሆነም ገልፀዋል።
በሜሮን ንብረት