ከሳርቤት-ጀርመን አደባባይ-ጋርመንት ፉሪ የሚዘልቀው የኮሪደር ልማት የነዋሪውን ፍላጎትና ጥያቄዎች የመለሰ፣ የገባነውን ቃል በተግባር የፈጸምንበት ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለፁ።
በኮሪደር ልማቱ ማኅበረሰቡ ቋሚና ዘላቂ የሥራ ዕድል እንዲያገኝ ተደርጓል ያሉት ከንቲባ አዳነች፤ ከ1 ሺ 100 በላይ ሱቆችን በመገንባት በጉሊት ሲሰሩ የነበሩ እናቶች በዘመናዊ ሱቅ ውስጥ እንዲነግዱ ዕድል መፈጠሩን አስታውቀዋል።
ኮሪደሩ ከካዛንቺስ ኮሪደር ቀጥሎ ረጅሙና ሰፊው ኮሪደር መሆኑን ጠቁመው፤ በርካታ የከተማ መልሶ ማልማት ሥራ የተሰራበት እንደሆነም ተናግረዋል።
በኮሪደሩ የወንዝ ልማት ሥራ ወንዞች የጤና ጠንቅ ሆነው የከረሙበትን ታሪክ መቀየር ተችሏል ብለዋል።
የኮሪደር ልማቱ አረጋውያንን፣ ሕፃናትን፣ ወጣቶችን፣ አካል ጉዳተኞችን እና የሥራ ዕድል የሚፈልጉ ዜጎችን ሁሉንም ያካተተ፣ ኢኮኖሚን የሚያነቃቃ ነው ብለዋል።
የሕዝብ ሀብት የሆነው የኮሪደር ልማት ከትውልድ ትውልድ እንዲሸጋገር ሁሉም ዜጋ በአግባቡ እየጠበቀ ሊጠቀምበት እንደሚገባም ጠቁመዋል።
ይሄ ሁሉ ሥራ ያለ ኅብረተሰቡ ድጋፍ አልተሰራም ያሉት ከንቲባ አዳነች፤ ዐለሠራተኞቻችን ውኃ እያቀረቡ "አይዟችሁ በርቱ" ላሉን፣ ሕንፃ እና ሱቆቻቸውን በማደስ እና በማፅዳት ለተባበሩት ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ቀን ከለሊት በመሥራት ምሳሌ በመሆን ውብ የሆነችውን አዲስ አበባ በመገንባት በኩል ላሳዩት የአመራር ሰጪነት እና ለአበረከቱት የሥራ ባህል ዕድገት እናመሰግናለን ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናግረዋል።
በሄለን ተስፋዬ