Search

በዚህ መንግሥት ውስጥ መሥራቴ ኢትዮጵያን በተሻለ እንዳውቅ አድርጎኛል - በለጠ ሞላ (ዶ/ር)

ቅዳሜ ጥቅምት 15, 2018 43

በዚህ መንግሥት ውስጥ መሥራት በመቻላቸው ኢትዮጵያን በተሻለ እንዲያውቁ እና አቅሟንም እንዲረዱ እንዳስቻላቸው የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (/) ተናገሩ፡፡

የኮይሻ ግድብን እና የአካባቢውን ልማት አስመልክተው አስተያየት የሰጡት ሚኒስትሩ፤ ከሁለት ዓመት በፊት ቦታውን መጎብኘታቸውን አስታውሰው አካባቢው በከፍተኛ ሁኔታ እየተለወጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

በአካባቢው ያለው የጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ አዲስ የቱሪዝም ሀብት መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሩ፤ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ተመሳሳይ የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎች ለምተው ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ድጋፍ እያደረጉ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በሥራ ምክንያት ወደ ተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ሲንቀሳቀሱ ያላወቁትን ለማወቅ እና ኢትዮጵያ ያላትን ሰፊ ሀብት እና አቅም ማየታቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ከዚህ በፊትም ሁሉም ሀብት ነበረን ያሉት ሚኒስትሩ፣ ሀብቶቹን ወደ ተጨባጭ እውነታ ለመለወጥ ግን እይታ ያስፈልግ እንደነበር ጠቁመዋል፡፡

አሁን እንደተጀመረው ይህን ኢትዮጵያ ያላትን ሀብት ለይቶ ወደ ተጨባጭ እውነታ መለወጥ መቻሉ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ አቅም ከፍ እንደሚያደርግ ገልፀዋል፡፡

የኮይሻ ግድብ በአፍሪካ ውስጥ ካሉ ትላልቅ ግድቦች አንዱ እንደሆነ የጠቀሱት ሚኒስትሩ፣ ሥራው በየጊዜው ተጨባጭ ለውጥ እያሳየ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

"ኢትዮጵያ ውስጥ እዚህም እዚያም ችግሮች አሉ" ያሉት ሚኒስትሩ፤ በሌላው የአፍሪካ ሀገር ቢሆን መንግሥት እየተሠሩ ያሉትን ፕሮጀክቶች ለማቋረጥ ችግሮቹ በቂ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ነገር ግን እጅን አጣጥፎ ከመቀመጥ በችግር ውስጥም ሆኖ አቅምን በመጨመር ለኢትዮጵያ የሚመጥኑ ታላላቅ ፕሮጀክቶች በመሥራት ስኬታማ መሆን መቻሉን አመልክተዋል፡፡

እየተማርን፣ የተሻለ ሥራም እየሠራን ለሀገራችን የምንችለውን ማበርከታችንን እንቀጥላለን ሲሉም አክለዋል ሚኒስትሩ፡፡

በለሚ ታደሰ

#EBC #EBCdotstream #PMOEthiopia #AbiyAhmedAli #Koysha #dam