የአማራ ክልል መንግሥት እና የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባላት የምክክር መድረክ በባህርዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።በመድረኩ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ዋና ኃላፊ እና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ እንዲሁም የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች እና በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮች እየተሳተፉ ይገኛሉ።
አቶ አደም በመድረኩ ባስተላለፉት መልዕክት፥ በኢትዮጵያ በምክክር እና በፉክክር ላይ መሠረት ያደረገ የዳበረ የፖለቲካ ሥርዓት እየተገነባ ይገኛል ብለዋል።
ጠንካራ ሕገ መንግሥት እና ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን ጨምሮ የሕግ ማዕቀፎች፣ ተቋማዊ አደረጃጀቶች እና ሌሎች አስቻይ ሁኔታዎች መፈጠራቸውን ገልጸዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች እርስ በርስ የሚመካከሩበት፣ ሌሎች ፓርቲዎች ገዢውን ፓርቲ የሚሞግቱበት፣ የምክክር እና የፉክክር ሚዛንን የጠበቀ ጤናማ የፖለቲካ ምህዳር መፈጠሩን አክለዋል።
ፓርቲዎች የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ ሕግ እና ሥርዓትን አክብረው በመንቀሳቀስ ለሀገራዊ ሰላም እና መረጋጋት የድርሻቸውን ማበርከት እንደሚገባቸው አመላክተዋል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ በበኩላቸው፥ ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ በኢትዮጵያ የዳበረ የፖለቲካ ሥርዓት ለመገንባት ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ጠቅሰው፤ ሰላማዊ አማራጭን በመጠቀም የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎችም ለዳበረ የፖለቲካ ልምምድ አዎንታዊ ሚናቸውን እየተወጡ እንደሚገኙ አክለዋል።