Search

በመኸር ወቅት ከተዘራው 4.5 ሚሊዮን ሄክታር ስንዴ፣ 2.9 ሚሊዮን ሄክታር የሚሆነው በክላስተር ዘዴ የለማ ነው

እሑድ ጥቅምት 16, 2018 50

“የስንዴ ምርት እና ምርታማነት ዕድገት ለሀገር ሉዓላዊነት” በሚል ዛሬ በተካሄደ ሀገር አቀፍ የስንዴ ልማት የመስክ ቀን በግብርና ሚኒስትሩ አዲሱ አረጋ የተመራ ከፍተኛ ልዑክ በምዕራብ አርሲ ዞን በክላስተር እየለማ ያለ የስንዴ ማሳ ጎብኝቷል።

በ2017/18 ዓ.ም የመኸር ምርት ዘመን እንደ ሀገር 20.7 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን የገለጹት አቶ አዲሱ፤ ከዚህ ውስጥ 4.5 ሚሊዮን ሄክታር የሚሆነው በስንዴ ሰብል የተሸፈነ መሆኑን ተናግረዋል።

ከ4.5 ሚሊዮን ሄክታር የስንዴ ማሳው ውስጥ 2.9 ሚሊዮን ሄክታር የሚሆነው በክላስተር የለማ መሆኑን አክለዋል።

እንደ ሀገር የስንዴ ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ገልጸው፤ በዚህም ከውጭ ይገባ የነበረውን የስንዴ ምርት በሀገር ውስጥ ምርት መሸፈን ተችሏል ብለዋል።

ምርት እና ምርታማነትን ለመጨመር በአሲዳማነት የተጠቃ አፈርን በኖራ የማከም ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም ጠቅሰው፤ በቀጣይ 8 የኖራ ፋብርካዎችን ለመገንባት እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።

በኦሮሚያ ክልል፣ ምዕራብ አርሲ ዞን፣ ዶዶላ እና አዳባ ወረዳዎች በተካሄደው የኩታ ገጠም ስንዴ ማሳ ጉብኝት የግብርና ሚኒስትር አዲሱ አረጋን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች፣ የክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊዎች እና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

በሂሩት እምቢአለ

#ebcdotstream #ethiopia #wheat