ዛሬ ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለኤክስፖርት ተመራጭ የሆነው የሀስ አቮካዶ ዝርያ፣ የችርቻሮ ዋጋው በኪሎ ግራም ከ4 እስከ 7 የአሜሪካ ዶላር ነው። በአሜሪካ፣ ካናዳ እና አንዳንድ የአውሮፓ ሀገራት አንድ ትልቅ የአቮካዶ ፍሬ እስከ አንድ የአሜሪካ ዶላር ድረስ ይሸጣል።
በዚህም የአቮካዶ ምርት በዓመት ከ18 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚንቀሳቀስበት ሰፊ የገበያ ፍላጎት ያለው ምርት ሆኗል።
በተለይ ካለፉት አስር ዓመታት ጀምሮ የዚህ ምርት ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሚገኝ ሲሆን፣ ይህን ተከትሎም እንደ ሜክሲኮ ላሉ የዓለማችን ቀዳሚ አምራች ሀገራት የአቮካዶ ምርት ሁነኛ የውጭ ምንዛሪ ምንጭ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።
በዓመት ከ1.28 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን በላይ የሚሆን የአቮካዶ ምርት ወደ ውጭ የምትልከው ሜክሲኮ፣ እ.አ.አ. በ 2024 ዓ.ም ከ3.7 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት ችላለች።
በኢትዮጵያም በተለይ ባለፉት 4 ዓመታት ይህን ምርት በስፋት ለማምረት ታቅዶ አመርቂ ውጤት የተገኘበት ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም ለሀገር ውስጥ ፍጆታ ብቻ ይውል የነበረውን የአቮካዶ ምርት ወደ ውጭ በመላክ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ ማግኛ እየሆነ ነው።
ሆኖም ኢትዮጵያ ካላት አቅም አንጻር ከምርቱ ማግኘት ያለባትን ጥቅም ሳታገኝ በመቆየቷ፣ በቀጣይ 15 ዓመታት ሀገሪቱን የዓለማችን ቀዳሚ የአቮካዶ አምራችና ላኪ ሀገር ለማድረግ የሚያስችል ብሔራዊ የአቮካዶ ልማት ፕሮግራም ይፋ ተደርጓል።
በዚሁ መሠረት 38.5 ቢሊዮን ብር በጀት በመመደብ ወደ ሥራ መገባቱም ተገልጿል።
ፕሮግራሙ ምርቱን አሁን ካለበት 100 ሺህ ሄክታር ወደ 191 ሺህ ሄክታር ለማድረስ፣ አጠቃላይ ምርቱንም ከ400 ሺህ ቶን ወደ 3.8 ሚሊዮን ቶን ከፍ ለማድረግ ያለመ እንደሆነ ታውቋል።
3 ሚሊዮን ባለአነስተኛ ይዞታ አርሶ አደሮች ከፕሮግራሙ ተጠቃሚ እንደሚሆኑም ተመላክቷል።
ቀደም ባሉት ጊዜያት የአቮካዶ ምርት ለምግብነት እና ለውበት መጠበቂያ ምርቶች መሥሪያ እንደ ዋንኛ ግብዓት ያገለግል የነበረ ሲሆን፣ አሁን ላይ ደግሞ ትላልቅ የአግሮ ፕሮሰሲንግ እና የመድኃኒት ፋብሪካዎች በግብዓትነት እየተጠቀሙበት ይገኛሉ።
በዋሲሁን ተስፋዬ