በክልሉ በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋዎች ለችግር የሚጋለጡ ዜጎችን ለመታደግ የተለያዩ የልማት ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ገለፀ።
ኮሚሽኑ በአሶሳ ዞን በሦስት ማዕከላት የተቀናጁ የግብርና ልማት ሥራዎችን እያከናወነ ሲሆን፣ በ270 ሔክታር ማሳ ላይ በቆሎ፣ ማሽላ እና የተለያዩ አዝርዕቶችን በማልማት ላይ መሆኑ ተመላክቷል።

የሰብል ልማት ሥራው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ወ/ሮ አስካለች አልቦሮ እና የብልፅግና ፓርቲ የክልሉ ቅርንጫፍ ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ኢስሀቅ አብዱልቃድር እና የክልሉ ከፍተኛ የሥራ አመራሮች በተገኙበት ተጎብኝቷል።
አመራሮቹም ኮሚሽኑ ያከናወናቸው የኩታ ገጠም የሰብል ልማት ሥራዎች የሚበረታቱ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የክልሉ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽነር አቶ መሐመድ አብዱልአዚዝ፣ ኮሚሽኑ በተለያዩ ምክንያቶች ተረጂ የሆኑ ዜጎችን መልሶ የማቋቋም ሥራ ሲያከናውን መቆየቱን አስረድተዋል።
ኮሚሽኑ ከተለያዩ አካላት የሚገኙ ድጋፎችን በማሰባሰብ እርዳታ ሲያደርግ መቆየቱን የገለጹት አቶ መሐመድ፤ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ የሰብል ምርትን በማሳደግ ሰብዓዊ ድጋፎችን በውስጥ አቅም ለመተካትና ተረጂዎችን ለማቋቋም እየሠራ መሆኑን አስታውቀዋል።
በጀማል አህመድ