Search

የአፍሪካ አገራት የጣና ፎረም ምክረ ሀሳቦችን በመተግበር ለአህጉሪቷ ለውጥ በቁርጠኝነት እንዲሰሩ ጥሪ ቀረበ

እሑድ ጥቅምት 16, 2018 33

የአፍሪካ አገራት የጣና ፎረም ምክረ ሀሳቦች በመተግበር ለአህጉሪቷ ለውጥ በቁርጠኝነት እንዲሰሩ የማላዊ የቀድሞ ፕሬዚዳንትና የጣና ፎረም የቦርድ አባል ጆይሴ ባንዳ ጥሪ አቀረቡ።
በባህር ዳርና አዲስ አበባ ከተሞች ላለፉት ሦስት ቀናት ሲካሄድ የቆየው 11ኛው ከፍተኛ ደረጃ ጣና ፎረም ዛሬ ተጠናቋል።
"አፍሪካ በተለዋዋጩ ሉላዊ ሥርዓት" በሚል መሪ ሀሳብ የተካሄደው ፎረም፤ በአፍሪካ ሠላምና ደህንነት ጋር በተያያዘ ያሉ ችግሮች፣ የመፍትሄ አቅጣጫዎች ላይ በትኩረት መክሯል።
አፍሪካ በኢኮኖሚ እንዴት ራሷን መቻል አለባት? ምን ዓይነት እርምጃዎች ያስፈልጋሉ? የሚሉ ጥያቄዎች ተነስተው ውይይት ተደርጓል።
በአፍሪካ ያሉ ወጣቶችና ሴቶችን ጨምሮ አካታች ሥርዓት መዘርጋት ለነገ የሚባሉ ጉዳዮች እንዳልሆኑ በፎረሙ በሰፊው ምክክር ተካሂዶበታል።
የማላዊ የቀድሞ ፕሬዚዳንትና የጣና ፎረም የቦርድ አባል ጆይሴ ባንዳ በፎረሙ መዝጊያ ላይ እንዳሉት፤ 11ኛው የጣና ከፍተኛ ደረጃ ፎረም ስኬታማ ሆኖ ተጠናቋል።
የፎረሙ መሪ ሀሳብ አፍሪካ በተለዋዋጩ ሉላዊ ሥርዓት እንደ አህጉር ልንነጋገርበት የሚገባ ወቅቱን የጠበቀ ጽንሰ ሀሳብ ነው ሲሉም ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት ወደ ዲጂታል የሚደረገው ሽግግር፣ የተፈጥሮ ሀብትን በፍትሃዊነት እና ዘላቂነት ተደራሽ ማድረግ ትኩረት የሚፈልግ ጉዳይ መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተዋል።
ዓለም በፍጥነት እየተለወጠች መሆኑን አስታውሰው፤አፍሪካም እየተለወጠ ላለው የዓለም ሥርዓት የሚመጥን እንቅስቃሴ ማድረግ አለባት ብለዋል።
ለዚህ ደግሞ በጣና ፎረም የሚቀርቡ ምክረ ሀሳቦችን ወደ ተግባር በመቀየር ረገድ ከአፍሪካ አገራት በቁርጠኝነት መሥራት ይጠበቃል ሲሉ አመላክተዋል።
አፍሪካ ለማሳካት ያስቀመጠቻቸው ውጥኖች ያለ ወጣቶች ተሳትፎ እውን ሊሆን እንደማይችል አመልክተው፤በአፍሪካ በሁሉም መስክ የሚከናወኑ ተግባራት ወጣቶችን ማዕከል ያደረጉ ሊሆኑ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በፎረሙ ላይ የተለያዩ አገራት ዲፕሎማቶች፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች፣ ልዩ መልዕክተኞች ምሁራንን ጨምሮ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።