የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኢኮኖሚያዊ እና አካባቢያዊ ፋይዳው ለጎረቤት ሀገራት ጭምር የተረፈ መሆኑን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር አምባሳደር ዘሪሁን አበበ ገለጹ።
ኢትዮጵያ ቀጣናዊ የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ከሕዳሴ ግድቧ ለጎረቤት ሀገራት ኃይል እያቀረበች መሆኗን ነው አምባሳደር ዘሪሁን ከኢቲቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ ያነሱት።
ለአፍሪካ ሕብረት መመሥረት የኢትዮጵያን ያክል ትልቅ ሚና የተጫወተ ሀገር አለመኖሩን የጠቀሱት አምባሳደር ዘሪሁን፤ ሀገሪቱ አሁንም ለቀጣናው ሰላም እና ልማት ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተች እንደምትገኝ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲም ለጎረቤት ሀገራት ቅድሚያ የሚሰጥ እንደሆነ ዳይሬክተሩ አክለዋል።

የቀጣናው ሀገራት የተለያዩ ግድቦችን በሚገነቡበት ወቅት ጎረቤት ሀገራትን የማማከር ልምድ እንዳልነበራቸው አንስተው፤ ኢትዮጵያ ግን ታላቁ የሕዳሴ ግድብን ስትገነባ ዲፕሎማሲያዊ አካሄድን መከተሏን ተናግረዋል።
ይህ አካሄድ ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት ያላትን ቁርጠኝነት እንዲሁም ታላቁ የኢትየጵያ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካውያን ጭምር መሆኑን ያሳየ ነው ብለዋል።
አንድ ሀገር የኃይል አቅርቦቱን ካላሟላ ምንም ዓይነት ዕድገት ሊያስመዘግብ እንደማይችል የአፍሪካ ሕብረት አጀንዳ 2063ን ዋቢ በማድረግ የተናገሩት አምባሳደር ዘሪሁን፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከአጀንዳ 2063 ዕቅዶች ጋር የተጣጣመ ፕሮጀክት ነው ብለዋል።

ዓባይ እና ቀይ ባሕር የኢትዮጵያ ፈተና ሆነው ለረጅም ጊዜ መቆየታቸውን ጠቅሰው፤ ሆኖም ግን በሁለቱ ላይ ጠንክራ ከሠራች መጻኢ ዕድሏ ይበልጥ የሰመረ እንደሚሆን አመላክተዋል።
የኢትዮጵያ መጠናከር ጂኦፖለቲካዊ ጥቅማቸውን እንደሚያሳጣቸው የሚያስቡ ታሪካዊ ጠላቶቿ በሀገሪቱ ሰላም እንዲደፈርስ እንደሚሠሩ ጠቅሰው፤ ሰላሟን በመጠበቅ የልማት ትልሞቿን ማሳካት ቅድሚያ የምትሰጠው ጉዳይ እንደሆነ ገልጸዋል።
በሜሮን ንብረት
#etv #ebcdotstream #ethiopia #geopolitics #ዓባይ #gerd #redsea #ቀይባሕር