Search

ግብርናውን ለማሸጋገር ላቅ ያለ ሚና እንደሚኖረው የታመነበት የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ

ረቡዕ ጥቅምት 19, 2018 40

ኢትዮጵያ በየዓመቱ በአማካኝ ከ1.5 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን በላይ የተለያዩ የአፈር ማዳበሪያዎችን ከውጪ ሀገራት ታስገባለች።
ሀገሪቱ ከውጭ የምታስገባውን የአፈር ማዳበሪያ በሀገር ውስጥ ለመተካት አቅዳ በ2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ወጪ የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ ጥላለች፡፡
በኢትዮጵያ ታሪክ ከፍተኛ ለውጥ እንደሚያመጡ ከታመነባቸው ሜጋ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ የሆነው ይህ ፋብሪካ በ3 ዓመት ጊዜ ውስጥ ሲጠናቀቅ፣ በዓመት እስከ 3 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የሚደርስ የአፈር ማዳበሪያ የማምረት አቅም እንደሚኖረው ተጠቁሟል፡፡
በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢኒስቲትዩት የግብርና ኢኮኖሚክስ ምርምር ዳይሬክተር እና ተመራማሪ የሆኑት ታደለ ማሞ (ዶ/ር) ከኢቲቪ ዳጉ ፕሮግራም ጋር ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ የአፈር ማዳበሪያ ከውጭ ወደ ሀገር ሲገባ የሚወስደው ሂደት ዘርፈ ብዙ ጫና እንዳለው አንስተዋል፡፡
ለአብነትም የማጓጓዣዎች ምቹ እና ቀልጣፋ አለመሆን፣ የውጭ ምንዛሬ እንዲሁም ሕገ ወጥ ደላሎች ተጠቃሽ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
የአፈር ማዳበሪ ፋብሪካው ተጠናቅቆ አገልግሎት መስጠት ሲጀምርም እነዚህን እና ሎሎች ችግሮችን በማቃለል ለምርታማነት እና ለሀገር ኢኮኖሚ የሚኖረው ሚና ላቅ ያለ እንደሚሆን ነው የገለጹት፡፡
በኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢኒስትቲዩት የግብርና ተመራማሪ የሆኑት ከፊና ኢፋ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የማዳበሪያ ፋብሪካው ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተናንሶ የሚታይ ጉዳይ አይደለም ብለዋል፡፡
ፋብሪካው ግብርናውን ለማሸጋገር ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ገልጸው፤ ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን እና ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ለጀመረችው ጥረት የበኩሉን አስተዋጽኦ ያደርጋል ነው ያሉት።
አያይዘውም የማዳበሪያ ፋብሪካው ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ ባሻገር፣ ለአፈር ማዳበሪያ ግዢ በየዓመቱ የሚወጣውን በቢሊዮን የሚቆጠር የውጭ ምንዛሪ እንደሚያስቀር ነው የጠቀሱት።
በሜሮን ንብረት እና ቢታንያ ሲሳይ