Search

ከአሜሪካ ኖርዝ ዳኮታ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ወደ ስልጤ ዞን ማሳዎች

ረቡዕ ጥቅምት 19, 2018 51

አብረሃም ትንሣኤ ይባላሉ፤ በሲቪል ምሕንድስና እና በግብርና ቴክኖሎጂ ከአሜሪካ ኖርዝ ዳኮታ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ተመርቀዋል።
እኚህ ሰው በአሜሪካ ሀገር የነበራቸውን ምቹ ኑሮ ትተው ወደ ሀገራቸው ኢትዮጵያ በመምጣት የምርጥ ዘር አቅርቦት ሥራ ላይ ተሰማርተዋል።
አቶ አብረሃም ‘የአሜሪካን ምቾት’ ትተው በዚህ ሥራ ላይ ለመሰማራት ምን አነሣሣቸው?
 
በኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ ምርታማነትን ለመጨመር ጥራት ያለው ምርጥ ዘር በሚፈለገው ወቅት አለማግኘት፣ የአቅርቦት እና ፍላጎት አለመጣጣም አንዱ እና ዋነኛው መሰናክል ነው።
አቶ አብረሃምም ይህንኑ ችግር ለመቅረፍ የምርጥ ዘር አቅርቦት ላይ ለመሰማራት መወሰናቸውን ከኢቲቪ ጋር ባደረጉት ቆይታ ተናግረዋል።
አሁን ላይ አባታቸው የመሠረቱትን ‘ትንሣኤ ዘርፉ የአዝርዕት ልማት ድርጅት’ በባለቤትነት እያስተዳደሩ ይገኛሉ።
የምርጥ ዘር አቅርቦት ላይ የተሰማራው ‘ትንሣኤ ዘርፉ የአዝርዕት ልማት ድርጅት’ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል፣ ስልጤ ዞን በሳንኩራ እና ሚቶ ወረዳዎች ሰፋፊ የእርሻ መሬት ወስደው ውጤታማነታቸው በምርምር የተረጋገጡ እና የአካባቢውን ሥነ-ምኅዳር ያገናዘቡ የስንዴ እና የበቆሎ ምርጥ ዘሮችን በማምረት የአርሶ አደሩን የምርጥ ዘር ፍላጎት ለማሟላት እየሠራ ይገኛል።
 
አቶ አብረሃም ከልጅነት ጀምሮ አባታቸው አቶ ትንሣኤ በባሌ እና ስልጤ ዞኖች ይሠሩት የነበረውን የግብርና ሥራ እያዩ ማደጋቸውን እና ለሥራው ፍቅር እንዳደረባቸው ይናገራሉ።
ለትምህርት በሄዱበት አሜሪካ ሀገርም አርፈው ለመኖር ያላስቻላቸው ይኸው ፍቅራቸው እንደሆነ እና ብዙ ሰዎች እዚያው አሜሪካ ይቀራል ብለው ቢያስቡም ወደ ሀገራቸው ተመልሰው የሚወዱት የእርሻ ሥራ ላይ መሰማራታቸውን ይገልጻሉ።
አሜሪካ ሀገር የተማሩትን ዘመናዊ የእርሻ ሥራ፣ እውቀት እና ቴክሎጂ አክለውበት ከአባታቸው ማሳ በመዝለቅ ውጤታማ ሥራም እየሠሩ ይገኛሉ።
ዛሬ ላይ ‘ትንሣኤ ዘርፉ የአዝርዕት ልማት ድርጅት’ ከማዕካለዊ ኢትዮጵያ እና ከኦሮሚያ ክልሎች ምርጥ ዘር ድርጅቶች ጋር በመተባበር የስንዴ እና በቆሎ ምርጥ ዘር እያቀረበ ነው።
የግብርና ሥራ በእውቀት ላይ የተመሠረተ መሆን እንዳለበት የሚገልጹት አቶ አብረሃም፣ መዳረሻችንን ማወቅ፣ እንዴት እንደምንሠራ መረዳት፣ የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች በብልሃት ለማለፍ ቀድሞ መዘጋጀት፣ ኪሳራዎችን ለመቋቋም እና ለመተካት ይረዳናል ይላሉ።
የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ቴዎድሮስ ታደሰ በበኩላቸው፣ ድርጅቱ የተለያዩ ድርቅ እና በሽታዎችን መቋቋም የሚችሉ ምርጥ ዘሮችን በእርሻ ማሳው ላይ እንደሚያመርት ገልጸዋል።
ድርጅቱ እርሻን በትራክተር የማረስ፣ ዘር በመስመር የመዝራት፣ የሰብል እንክብካቤ እና አያያዝ፣ በቴክሎጂ የተደገፈ የምርት አሰባሰብን በተመለከተ ለአካባቢው አርሶ አደሮች የቴክሎጂ እና የእውቀት ሽግግር በማድረግ ላይ ይገኛልም ብለዋል።
የእርሻ ድርጅቱ ለ50 ዜጎች ቋሚ እና ከ400 በላይ ለሚሆኑት ደግሞ ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፍጠሩንም አቶ አብረሃም ገልጸዋል።
 
በመሐመድ ፊጣሞ