Search

ብር አስቀምጦ ከተማ ቤት መሥራት ብቻ ሳይሆን በገጠርም ሞዴል ቤቶችን መሥራት ያስፈልጋል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ረቡዕ ጥቅምት 19, 2018 73

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን በኦሮሚያ ክልል፣ ምስራቅ ሸዋ ዞን ጉብኝት አድርገዋል።
ጉብኝቱ በክረምት የስንዴ ምርት ሥራዎች የተገኘውን ውጤት የምርት አሰባሰቡን በመመልከት ለመገምገም እና የበጋ ስንዴ ሥራ ማስጀመር ላይ ያተኮረ መሆኑንም አስታውቀዋል።
 
በወቅቱም ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደተናገሩት፤ ምንም እንኳን ነባሩ ባህላዊ የግብርና ዘዴ አሁንም ቢኖርም፣ በሰፊው ለማረስ የሚያስችለው ሜካናይዜሽን እያደገ በመምጣቱ የግብርና ምርታማነት እየጨመረ ይገኛል።
ኅብረተሰቡ በጓሮው፣ በማሳው እንዲሁም በክረምትና በበጋ ሥራዎች ላይ እንደሚሳተፍ ጠቅሰው፣ ይህንን እንቅስቃሴ ከማሳ ወደ ቤት ማምጣት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።
አርሶ አደሮች ገንዘብ በባንክ የማስቀመጥ ልምዳቸው እያደገ መምጣቱን ጠቁመው፣ ነገር ግን የኑሮ ደረጃቸውንና ቤታቸውን ማሻሻል እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።
አቅም ያላቸው አርሶ አደሮች ገንዘብ አስቀምጠው ከተማ ቤት ከመስራት ይልቅ፣ በገጠር የተገነቡ ሞዴል ቤቶችን መሰረት በማድረግ ዘመናዊ ቤቶችን መሥራት እንዳለባቸውም መልዕክት አስተላልፈዋል።
 
በቢታኒያ ሲሳይ