ኢትዮጵያ ዘመናዊ የግብርና መሣሪያዎችን በስፋት ወደሥራ እያስገባች መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለፁ።
የገጠር ሽግግርን ለማረጋገጥ አንዱ መንገድ የግብርና ማሽኖችን ማበራከት መሆኑን ጠቁመው፤ ለዚህም ባለፉት ጥቂት ዓመታት ከ150 ሺ በላይ የውኃ መሳቢያ ፓምፖች ወደ ሀገር ውስጥ መግባታቸውን አስታውቀዋል።

በተጨማሪ 10 ሺ የሚገመቱ ትራክተሮች ወደ ሥራ ገብተዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ወደ 1 ሺህ የሚጠጉ ኮምባይነሮች ሥራ ላይ መዋላቸውንም ገልጸዋል።
የውኃ መሳቢያ ፓምፖች እና ትራክተር ከውጭ ማምጣት ብቻ ሳይሆን በሀገር ውስጥ መገጣጠም መጀመሩንም አመላክተዋል።
አሁንም በበሬ የሚያርሱ አርሶ አደሮች ቢኖሩም ማሽኖች በስፋት እየቀረቡ መሆኑን አንስተዋል።

ዘንድሮ በሀገር አቀፍ ደረጃ በክረምት ወደ 4.5 ሚሊዮን የሚጠጋ ሔክታር ላይ የስንዴ ልማት ተከናውኗል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በዚህ ዓመት ከ8.5 እስከ 9 ሚሊዮን ሔክታር ላይ ስንዴ ይመረታል ብለዋል።
ከስንዴ በተጨማሪ የፓፓያ እና የሙዝ ዝርያዎችን ከውጭ በማምጣት፣ ከዚህ በፊት የነበረው ተሻሽሎ በአዲሱ ዝርያ በመተካቱ ምርታማነቱ ከፍተኛ መሆኑንም አስታውቀዋል።
በቢታኒያ ሲሳይ