ኢትዮጵያ ትበለፅጋለች፣ ትቀየራለች፣ በሚቀጥሉት አስርት ዓመታትም በአፍሪካ ያላት ቦታ ይስተካከላል ሲባል ፍላጎት ብቻ ሳይሆን መሬት ላይ ያሉ ሥራዎችን በማየት ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ።
በብዝሃ ዘርፎች እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች የኢትዮጵያን ብሩህ ተስፋ የሚያመላክቱ መሆናቸውንም አንስተዋል።

ሁሉንም ዘርፎች እኩል በማስኬድ በተጨባጭ ትሩፋት መገኘቱን ጠቁመው፤ ዋና ዋና ዘርፎችን ይዘን ሌሎች ዘርፎችንም እያሰናሰልን ነው፤ በመሆኑም ይበልጥ እንሥራ ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የማዕድን ዘርፉን እና የኢንዱስትሪ ዘርፉን በማስተሳሰር ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ ሃብት እንደሚገኝ ጠቁመው፤ አርሶ አደሩ የሚጠቀምበትን የአመራረት መንገድ ዘመናዊ ማድረግ ከተቻለም የኢትዮጵያ ብልፅግና እንደሚሳካ ገልጸዋል።
ምርታማነት ሲያድግ ገበያ ይረጋጋል፣ ገቢ ይጨምራል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በዚህም ከውጭ የምናስገባቸው ምግቦች ይቀንሳሉ እንዲሁም ወደ ውጭ የመላክ አቅምም ይጨምራል ሲሉ አስረድተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው፤ እንሥራ፣ እንበርታ፣ ከአልባሌ ቦታ ወጥተን በሥራና በትጋት ብቻ ውጤት ለማምጣት እንጣር ብለዋል።
በቢታኒያ ሲሳይ
 
                                                 
                                                                 
                                                                 
                                                                 
                                                                 
                                            