Search

1.5 ሚሊዮን ቤቶችን ለመገንባት እንቅስቃሴ ተጀምሯል

ሓሙስ ጥቅምት 20, 2018 61

መንግሥት የዜጎችን የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ለማሟላት በሚቀጥሉት ሥድስት ዓመታት ውስጥ 1.5 ሚሊዮን ቤቶችን ለመገንባት አቅዶ እንቅስቃሴ መጀመሩን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ምላሽ እና ማብራሪያ 1.5 ሚሊዮን መኖሪያ ቤቶችን ለመገንባት የተቀረጸው ፕሮጀክት በመላው ሀገሪቱ የሚተገበር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
እያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ የቤት ባለቤት ማድረግ የሚቻል ባይሆንም፣ ዜጎች በአቅማቸው ተከራይተው ለመኖር የሚችሉበትን የቤት አማራጭ እንዲያገኙ ለማድረግም እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
መንግሥት በሚቀጥሉት አምስት እና ሥድስት ዓመታት ከ30 ቢሊዮን ዶላር በላይ በሆነ ወጪ ሊተገብራቸው ካቀዳቸው ሰባቱ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ውስጥ አንዱ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ነው፡፡
ለዚህም መንግሥት መሰረተ ልማቶችን እያሟላ እንደሚገኝ የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለቤቶቹ ግንባታ የሚያስፈልጉ መሠረታዊ ግብዓቶች በሀገር ውስጥ እንዲመረቱ የማድረግ ሥራ ሲሠራ መቆየቱን ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያን የቤት ፍላጎት ለማሟላት የሚያስችሉ አምራች ድርጅቶችን የማስፋፋት እና በሀገር ውስጥ የማይመረቱ የነበሩ ምርቶችን በሀገር ውስጥ እንዲመረቱ የማድረግ ተግባራት ሲከናወኑ መቆየታቸውንም አክለዋል፡፡
ለቤቶች ግንባታ ትልቅ አቅም የሚሆኑትን የሲሚንቶ፣ ብረት ማምረቻ እና የመስታውት ፋብሪካዎችን የማስፋፋት እና የማጠናከር ሥራዎችም እየተሰሩ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አያይዘው ግራናይት፣ ማርብል እንዲሁም የፈርኒቸር ሥራዎች ላይ ሰፋፊ ዝግጅቶች መደረጋቸውንም አንስተዋል፡፡
በቅርቡም ማሳያ የሚሆኑ ቤቶች እንደሚገነቡም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አመላክተዋል፡፡
በንፍታሌም እንግዳወርቅ