ብዙ ሥራ ይጠበቅብናል፣ ነገር ግን በስንዴ ምርት የሚታየው ውጤት ተስፋ ሰጪና አስደማሚ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተናገሩ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትናንትናው ዕለት በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን የግብርና ሥራዎችን ጎብኝተዋል።

ከጉብኝታቸው በኋላ በሰጡት ማብራሪያም፤ ባለፉት ዓመታት ለግብርናው ዘርፍ ትኩረት በመስጠት የስንዴ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ በተሠራው ሥራ አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል ብለዋል፡፡
በዚህም ለስንዴ ግዢ ይውል የነበረውን ከ1ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ማስቀረት መቻሉን ነው የተናገሩት፡፡
በሀገሪቱ የሚከናወኑ የግብርና ሥራዎች ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን ገልጸው፤ በስንዴ ልማት አምና ከነበረው ላቅ ያለ ምርት ዘንድሮ እንደሚጠበቅ አመላክተዋል፡፡
ምርታማነት እያደገ ሲሄድ ገበያ ይረጋጋል፤ ገቢ ይጨምራል፤ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከውጪ የሚገቡ ምግቦችን በመቀነስ ወደ ውጭ የመላክ አቅማችን ያድጋል ብለዋል።
የግብርና ልማት ባለሙያዎች ከአርሶ አደሩ ጋር ይውላሉ፣ የወረዳና የዞን አመራሮች ሥራቸው የሚገመገመው የአርሶ አደሩን ሕይወት በመቀየር በሚያመጡት ውጤት ነው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
ከፍተኛ ምርት የሚያመርቱ አካባቢዎች አርሶ አደሩ በፍጥነት ወደ ዘመናዊ የኑሮ ዘይቤ እንዲሸጋገር ማገዝ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡
አርሶ አደሮች የኑሮ ደረጃቸውንና ቤታቸውን ማሻሻልና የእርሻ ሥራ ውጤቶች በሕይወታቸው ላይ በተግባር መታየት እንዳለበትም ነው የገለጹት።
አቅም ያላቸው አርሶ አደሮች በገጠር የተገነቡ ሞዴል ቤቶችን መሰረት በማድረግ ዘመናዊ ቤቶችን መሥራት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
ከዚህ ቀደም ግብርናን በዚህ መንገድ ብንመራው ኖሮ አሁን የምናየውን ውጤት ማየት እንችል ነበር ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በመሐመድ ፊጣሞ