Search

ባለ ሁለት አሐዝ እድገት እንደሚያስመዘግብ የሚጠበቀው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ

ሓሙስ ጥቅምት 20, 2018 52

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በያዝነው የ2018 በጀት ዓመት ባለ ሁለት አሐዝ እድገት ያስመዘግባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መግለጻቸው ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባሳለፍነው ዓመት 9.2 በመቶ ዓመታዊ እድገት ማስመዝገብ የቻለ ሲሆን፤ በያዝነው ዓመት ደግሞ 10.2 በመቶ እድገት እንደሚያስመዘግብ ይጠበቃል፡፡

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ አሶሴሽን ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና ከኢቲቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከግብርና መር ወደ ብዝሃ ዘርፍ እንዲሸጋገር የተነደፈው ፖሊሲ የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብ ማድረጉን ገልፀዋል፡፡

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) እና የዓለም ባንክ ባወጡት ትንበያ መሰረት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት ከአፍሪካ በከፍተኛ መጠን እያደገ የመጣ መሆኑን እንደሚያሳይ ፕሮፌሰር ጣሰው ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በዚህ መጠን ማደጉ በርካታ የስራ እድሎችን ከመፍጠሩ ባሻገር የኢኮኖሚ እንቅስቃሴው በከፍተኛ መጠን እንዲነቃቃ ማድረጉንም አንስተዋል፡፡

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በአንድ ዘርፍ ላይ ብቻ ትኩረቱን አድርጎ ከመስራት የብዝሐ ኢኮኖሚ ዕድገት መርህን መከተሉ የተሻለ ለውጥ እንዲመዘገብ አስተዋፅኦ ማበርከቱን ተናግረዋል፡፡

በመንግስት ተቀርፀው የተከናወኑ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ለኢኮኖሚው መሻሻል ያበረከቱት አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

ይህም ወደ ውጭ የሚላከውን ምርት በማብዛት የውጭ ምንዛሬን የጨመረ ሲሆን ከውጭ የሚገባውን በመቀነስ ኢኮኖሚውን ማረጋጋት መቻሉን ነው የተናገሩት፡፡

ለዘመናት ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ሳይገኝባቸው የነበሩ እንደ ማዕድን ያሉ ዘርፎች አሁን ላይ ከፍተኛ የሆነ ለውጥ እያመጡ እንደሚገኙ አንስተው፤ እነዚህም ለኢኮኖሚው መሻሻል ከፍተኛ ድርሻ እንዳበረከቱ ተናግረዋል፡፡

የታዩ ለውጦችን በቀጣይነት ለማስቀጠልም መሰረታዊ የሆኑ የኢኮኖሚ መዋቅሮችን ማሻሻል፣ የፋይናንስ ሥርአትን ማጠናከር እንዲሁም የባንክና የብድር የአሰራር ስርዓቶችን ማሻሻል በስፋት ሊሰራበት እንደሚገባ አንስተዋል፡፡

አቶ መስፍን አያይዘውም ኢትዮጵያ በርካታ የሰው ሀይል ያላት ሀገር ብትሆንም በስልጠና የዳበረ የሰው ኃይልን ማጠናከር እንዲሁም ማብቃት ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡

በንፍታሌም እንግዳወርቅ

#EBC #ebcdotstream #Ethiopia #economy