በምሥራቅ ሸዋ ዞን የተከናወኑ የግብርና ሥራዎች አርሶ አደሮች ከተረጂነት ወደ አምራችነት እየተቀየሩ መሆናቸውን ያሳየ ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለፁ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን የግብርና ሥራዎችን ከጎበኙ በኋላ በሰጡት ማብራሪያ፤ አካባቢው ዝናብ አጠርና በሴፍቲኔት የሚረዳ እንደነበር ጠቁመው፤ በአካባቢው የሚያልፈውን አዋሽ ወንዝ በመጠቀም ዘርፈ ብዙ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።
መንግስት ትኩረት ሰጥቶ ባከናወናቸው ተግባራት የከርሰ ምድር ውኃን በማውጣት አካባቢውን ማልማት መቻሉንም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልፀዋል፡፡
ከተመረጡ ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርሞች መካከል ግብርና አንደኛው ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በግብርናው ላይ የሚከናወኑት ተግባራት ለአምራች ኢንዱስትሪው ትልቅ ግብአት ሆነው እንደሚያገለግሉ ተናግረዋል፡፡
አካባቢው ከተረጂነት ወደ አምራችነት የተቀየረ መሆኑን አንስተው፤ በአካባቢው የተለያዩ አትክልት እና ፍራፍሬ እንዲሁም አዝዕርትን ማምረት መቻሉን አንስተዋል፡፡
የተመረቱ ምርቶችን ለገበያ በማቅረብ በኩልም ለአካባቢው ማህበረሰብ በተመጣጠነ ዋጋ ማቅረብ መቻሉን ጠቅሰዋል፡፡
ይህ ተግባር የኢትዮጵያን የማንሰራራት ዘመን፤ የኢትዮጵያን ብልፅግና አይቀሬነት ማሳያ መሆኑንም ነው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት፡፡
በንፍታሌም እንግዳወርቅ
#EBC #ebcdotstream #Ethiopia #Agriculture