ኢትዮጵያውያን ከምን ጊዜውም በላይ አንድነታቸውን በማጠናከር የጠላት ሴራዎችን ሁሉ መመከት እንዳለባቸው የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር የሆኑት ጥላሁን ተፈራ (ዶ/ር) ገለፁ።
ጥላሁን ተፈራ (ዶ/ር) አክለውም፣ ኢትዮጵያ ጥቅሟን ለማስከበር በምትሰራቸው የኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ ሥራዎች ላይ የውጭ ተፅዕኖዎች ሲፈጠሩ እንደነበር አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ጠላቶች ለሀገሪቱ ውድቀት ቢበረቱም፣ ይህ ፈተና ሕዝቡን ሳይበግረው በአብሮነት ጠንካራ ሀገር ለመገንባት የጀመረውን ጥረት ቀጥሏል ሲሉም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት በተለያዩ ጊዜያት ቢፈተንም፣ ሕዝቡ በአብሮነት የሀገሩን ሉዓላዊነት ማስከበሩንም አስረድተዋል።
ኢትዮጵያውያን በዓድዋ ድል ያደረጉት እና ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ያጠናቀቁት ኅብረታቸው በመጠቀም መሆኑን አንስተው፤ አሁንም ዜጎች አንድነታቸውን አጠናክረው በመቀጠል ተጨማሪ ውጤቶችን ማስመዝገብ አለባቸው ብለዋል።
ኢትዮጵያውያን የአንድነት እሴቶችን በማስቀጠል ሀገራዊ የልማት ግቦች ላይ ያላቸውን ተሳትፎ ማጎልበት እንዳለባቸውም አመላክተዋል።
ለዘመናት የዘለቀውን የአብሮነት እና የመቻቻል እሴት ማጠናከር እንደሚገባም ገልጸዋል።
በቢታኒያ ሲሳይ
 
                                                 
                                                                 
                                                                 
                                                                 
                                                                 
                                            