የኢትዮጵያ አየር መንገድ 21ኛውን ኤርባስ A350-900 አውሮፕላን ዛሬ መረከቡን ገልጿል።
አየር መንገዱ ዛሬ የተቀበለው ኤርባስ A350-900 አውሮፕላን እጅግ ዘመናዊ እና እስከ 340 ሰዎችን መመጫን አቅም ያለው ነው።
አዲሱ አውሮፕላን አየር መንገዱ ለደንበኞች እየሰጠ ያለውን አስተማማኝና ምቹ አገልግሎት ይበልጥ የሚያጠናክር እና በአቪዬሽን ኢንዱስትሪው ያለውን የመሪነት ሚና የሚያስቀጥል ነው ተብሏል።
አፍሪካን ከዓለም በማገናኘት አንጋፋነቱን ማስቀጠል የቻለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደፊትም ሌሎች ኤርባስ A350-900 እጅግ ዘመናዊ አውሮፕላኖችን ለመቀበል በሂደት ላይ ይገኛል።
የስታር አሊያንስ አባል የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በመንገደኞች፣ በጭነት፣ በመስተንዶ፣ ለደንበኞች አስተማማኝ አገልግሎት በመስጠት በርካታ ሽልማቶችን ማሸነፉ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአቪዬሽን ኢንዱስትሪው ተወዳዳሪነቱን እና መሪነቱን ለማስቀጠል በ10 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በቢሾፍቱ የግዙፍ ዓለመ አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ለማካሄድ ቅድመ ዝግጅት እያደረገ ይገኛል።
በላሉ ኢታላ