ኢትዮጵያ በማዕድን ሀብት የበለጸገች ሀገር ብትሆንም በዘርፉ በሚገባው ልክ ሳትጠቀም ቆይታለች፡፡
ኢትዮጵያ በዓለም ተፈላጊነት ያላቸው ማዕድናት የሚገኙባት ሀገር ናት፡፡ ለምሳሌ በትግራይ የሚገኙ ሳፋየሮች፣ በኦሮሚያ የሚገኙ ኢሜራልዶች እንዲሁም በአማራ ክልል ወሎ እና ሰሜን ሸዋ የሚገኙ ኦፓሎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡
የማዕድን ዘርፉ ሀገሪቱ ካስቀመጠቻቸው አምስቱ የኢኮኖሚ ምሰሶዎች ውስጥ ተጠቃሽ ሲሆን፣ ዘርፉ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራበት ይገኛል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የማዕድን ዘርፍ ተመራማሪ እና ሥነ ምድር ትምህርት ክፍል ኃላፊ የሆኑት ባይሳ ረጋሳ (ዶ/ር) ከኢቲቪ አዲስ ቀን መሰናዶ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ኢትዮጵያ ለዘርፉ በሰጠችው ትኩረት የአዲስ ምዕራፍ ጅማሮ እና ተስፋዋ መታየት ጀምሯል ብለዋል፡፡
ዘርፉ የውጭ ምንዛሬን በማስገኘት እና ለዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር ረገድ ትልቅ አበርክቶ እንደሚኖረው ገልጸው፣ ለዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የበኩሉን አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል ነው ያሉት።
የማዕድን ዘርፉን በማሳደግ ሂደት ውስጥ መሰረተ ልማቱ አብሮ እንደሚያድግም አክለው ገልጸዋል፡፡
የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የማዕድን ሀብት ልማት ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ናስር መሐመድ በበኩላቸው፤ ክልሉ በበርካታ ማዕድናት የበለጸገ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ነገር ግን ከዚህ ቀደም እነዚህ የተፈጥሮ ሀብቶች የሆኑትን ማዕድናት በባህላዊ መንገድ በማውጣት ሂደት ለብክነት ይዳረጉ እንደነበር አንስተዋል፡፡
አሁን ላይ ለዘርፉ ልዩ ትኩረት በመስጠት እየተሰራበት እንደሆነ ገልጸው፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ በዘርፉ መሻሻል እንደታየ አመላክተዋል፡፡
በሜሮን ንብረት