የአሜሪካን ዶላር ኖት ጨምሮ ብዙ ሀገራት የሚያሳትሙት የገንዘብ ኖት ጥንካሬ እንዲኖረው እስከ 75 በመቶ የሚሆን የጥጥ ምርት ይቀላቀልበታል።
ለዘመናት ለጨርቃ ጨርቅና አልባሳትን ለመስራት ብቻ ይጠቅም የነበረው የጥጥ ምርት ከዚህ ባለፈ ጠፈርተኞች በህዋ ላይ የሚለብሱትን እጅግ ውድ የሆኑ አልባሳት ለመስራትም ተመራጭ ግብዓት ሆኖ ቆይቷል።
እንዲሁም ቀደም ባሉት ጊዜያት የመኪና ጎማዎች በሚመመረቱበት ወቅት ፋይበሩን ለማጠናከር የጥጥ ክሮች ጥቅም ላይ ይውሉ ነበር።
በተጨማሪም ከጥጥ የሚገኘው የጥጥ ዘር (Cottonseed) ከፍተኛ ጥራት ያለው የዘይት ምንጭ ሆኖ ያገለግላል። በዚህ ሂደት ተጣርቶ የሚቀረው ተረፈ ምርትም በፕሮቲን የበለጸገ በመሆኑ ለከብቶች እና ለሌሎች የቤት እንስሳት እንደ ዋና መኖነት ያገለግላል።
ይህም በመሆኑ ምርቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ በዓለም ገበያ ላይ ያለው ፍላጎት እየጨመረ መጥቷል።
ሀገራችን ኢትዮጵያ ለጥጥ ምርት የሚሆን ተስማሚ መሬት እና የአየር ፀባይ ካላቸው ሀገራት መካከል አንዷ ናት።
ጥናቶች እንደሚያሳዩት ኢትዮጵያ ከ2.6 ሚሊየን ሄክታር በላይ የሚሆን ለጥጥ ልማት ምቹ የሆነ መሬት ያላት ሲሆን፤ ከዚህ እምቅ አቅም ውስጥ ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው ከ3 በመቶ በታች የሆነ መሬት ነው፡፡
ይህ በመሆኑም በፍጥነት እያደገ ለሚገኘው የኢትዮጵያ የጨርቃ ጨርቅ እና አልባሳት ኢንዱስትሪ ግብዓት የሚውል የጥጥ ምርት የውጭ ምንዛሪ በማውጣት ከውጭ ማስገባት ግድ ሆኖ ቆይቷል።
መንግስት የዘርፋን ፍላጎት ለማሳደግ እና የጥጥ ምርትን ከሀገር ውስጥ ፍላጎት ጋር ከማጣጣም ባለፈ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለማድረግ የሚያስችል ዕቅድ ቀርጾ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።
በ2017/18 የምርት ዘመን ለጥጥ ምርት ተስማሚ በሆኑ ቆላማ አካባቢዎች ለማልማት በዕቅድ ከተያዘው 110 ሺህ ሄክታር መሬት በጥሬ ጥጥ 1.9 ሚሊየን ኩንታል የተገኘ ሲሆን፤ ወደ 66 ሺህ ቶን የተዳመጠ ጥጥ ማግኘት መቻሉን የግብርና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል፡፡
በተጨማሪም ከውጭ የሚገባውን የጥጥ ምርት በሀገር ውስጥ ከመተካት ባለፈ የውጭ ምንዛሪ ምንጭ ለማድረግ እየተተገበረ በሚገኘው ስትራቴጂ የተሻሻሉ የጥጥ ዘሮች ለአርሶ አደሩ እየተከፋፈለ ሲሆን፤ በቅርቡም የወረር ግብርና ምርምር ማዕከል ከ44 አይነት በላይ የጥጥ ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ አከፋፍሏል።
በዋሲሁን ተስፋዬ
#ebc #ebcdotstream #Ethiopia #Cotton