የዋጋ ግሽበትን በመቆጣጠር የኑሮ ውድነትን ከመቀነስ አንፃር ኅብረተሰቡ ላይ ጫና ለመፍጠር የሚሞክሩ ነጋዴዎችን ሥርዓት ለማስያዝ ታቅዶ የተከናወነው ሥራ ውጤት ማምጣቱን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
አንዳንድ ነጋዴዎች በዓላትን ጨምሮ በተለያዩ ሰበቦች ዋጋ በመጨመር ኅብረተሰቡን ላልተፈለገ የኑሮ ጫና መዳረጋቸውን ከንቲባ አዳነች በቅርቡ ለአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ባቀረቡት ሪፖርት አንስተዋል።
ይህን ችግር ለመቅረፍም ቁጥጥር ከማድረግ በተጨማሪ የገበያ ማዕከላት ተቋቁመው የደላላ ሰንሰለትን በማስቀረት ምርት ከአምራቹ በቀጥታ ለሸማቹ እንዲደርስ የማድረግ ሥራ ስለመከናወኑ ገልጸዋል።
በኅብረተሰቡ ጥያቄ መሠረት የኅብረት ሥራ ማኅበራትን በማጠናከር ሸማቹ ከገበያ ማዕከላት በጅምላም፣ በችርቻሮም መግዛት የሚችልበት ዕድልም ተፈጥሯል ብለዋል።
የኑሮ ውድነት ጫናን ለመቀነስ በጀት በመመደብ እና ትስስር በመፍጠር የኅብረት ሥራ ማኅበራት ምርቶችን ወደ ከተማ እንዲያስገቡ አድርገናልም ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስተር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሰጡት የሥራ አቅጣጫ መሠረት ከእያንዳንዱ ክልል ምርቶች ወደ ከተማ የሚገቡበትን ሰንሰለት የማሳጠር ሥራ ስለመሠራቱም ነው ከንቲባዋ የተናገሩት።
በዝቅተኛ ገቢ ለሚተዳደሩ የከተማዋ ነዋሪዎች በተለይ በበዓላት በተደረገ የማዕድ ማጋራት ከ500 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ተጠቃሚ መሆናቸውንም አንስተዋል።
የከተማዋ ባለሀብቶች ጭምር በስፋት የሚሳተፉበት፣ ልማድ እየሆነ የመጣው እና አብሮነትን የሚያጠናክረው ይህ የእርስ በርስ መተጋገዝ በጎ ምግባር ወደፊትም ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባው ጠቁመዋል።
በሄለን ተስፋዬ
#ebcdotstream #addisababa #inflation