ባለፉት ወራት ከ21.7 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሠብሰቡን የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ አስታወቀ።
በክልሉ ገቢዎች ቢሮ የግብር ትምህርት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ታዘባቸው ጣሴ ለኢቢሲ እንደገለፁት፤ እስከ ጥቅምት 25 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ከ21.7 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሠብስቧል።
ገቢው ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከ7 ቢሊዮን ብር በላይ ብልጫ አለው ብለዋል።
ለዚህም ውጤት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መሠራቱ እና በኤሌክትሮኒክስ የታክስ አስተዳደር ስርዓት የደረጃ "ሐ" ግብር ከፋዮች ግብራቸውን በአሉበት ሆነው እንዲከፍሉ መደረጉ ዋነኛ ምክንያቶች መሆናቸውን አንስተዋል።
ቢሮው ብልሹ አሰራሮችን ለማስተካከልና የአገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻል እየሰራ ሲሆን፣ የሥነ-ምግባር ጉድለት በታየባቸው 58 ባለሙያዎች ላይ የተለያየ እርምጃ መወሰዱንም አስታውቀዋል።
የደረሰኝ መሰወር፣ የግብር ማጭበርበር፣ የንግድ እንቅስቃሴ አለመረጋጋት እና የመሳሰሉ ተግዳሮቶች መኖራቸውን ጠቁመው፤ እነዚህን ችግሮች ለመፍታትም እየተሠራ መሆኑን ዳይሬክተሩ አንስተዋል።
በ2018 በጀት ዓመት ከ100.3 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሠብሰብ ታቅዶ እየተሠራ ነው ሲሉ ታዘባቸው ጣሴ ገልጸዋል።
በተስፋሁን ደስታ