Search

በሃሳብ ፉክክር የሚጸና ሀገር፦ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለኢትዮጵያ ህልውና!

ሓሙስ ጥር 28, 2018 38

7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች የፖሊሲ አማራጮቻቸውን ይዘው የሚፎካከሩበት መድረክ ብቻ ሳይሆን፣ እኛ እንደ ሀገር የፖለቲካና የዴሞክራሲ ሥርዓት ስብራታችንን የምንጠግንበት ወሳኝ የታሪክ ምዕራፍ ነው።

ዴሞክራሲ ሂደትም ውጤትም በመሆኑ፣ ይህ ምርጫ ስኬታማ እንዲሆን የሕዝብ ንቁ ተሳትፎና የሂደቱ ቅቡልነት ለኢትዮጵያ ዘላቂ ህልውና ወሳኝ መሠረት ነው።

እንደ ሀገር ካሉብን ዘመናዊ የፖለቲካ ተግዳሮቶች ለመውጣት፣ ቅቡልነት ያለው ሀገረ መንግሥት ለመገንባትና ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ በምርጫ ብቻ የሚመራ ሥርዓት መገንባት አማራጭ የሌለው መንገድ ነው።

ለምን በንቃት መሳተፍ ይኖርብናል?

የሰለጠነ የፖለቲካ ባህልን ለመገንባት፦ ምርጫ የሃሳብ ፉክክር የሚደረግበት የሰለጠነ ፖለቲካ መገለጫ እንጂ የጠብ መድረክ ባለመሆኑ፣ የዜጎች ተሳትፎ ይህን ባህል ያጸናል።

ቅቡልነት ያለው ሀገረ መንግሥት ለመመሥረት፦ ምርጫው የሕዝብ ሉዓላዊነት የሚረጋገጥበትና ለተመሠረተው መንግሥት ሙሉ ቅቡልነትን የሚሰጥ ዋነኛ መሣሪያ ነው።

ከውጤቱ በላይ ለሂደቱ ታማኝነት፦ የምርጫው ሂደት ነጻ፣ ሰላማዊና ፍትሐዊ ሆኖ መጠናቀቁ በራሱ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ትልቅ ድል ነው።

ለብሔራዊ ጥቅም መከበር፦ በምርጫው ወቅት በንቃት መሳተፍ የኢትዮጵያንን እውነተኛ የዴሞክራሲ ጉዞ በትልቁ የሚያጎላና ብሔራዊ ጥቅማችንን የሚያስከብር ተግባር ነው።

በምርጫ ሂደት ውስጥ የሚታይ የሃሳብ ፉክክር የዴሞክራሲ ውበት እንጂ የልዩነት ምንጭ  አይደለም። እያንዳንዱ ዜጋ ሂደቱን በባለቤትነት በመከታተል፣ የጥላቻ ንግግርንና ሐሰተኛ መረጃዎችን በመመከት ለሀገራዊ መግባባት መቆም ይኖርበታል።

ለኢትዮጵያ ከሰለጠነ የምርጫ ፉክክር ውጭ ሌላ አማራጭ የለም፤ ሰላማዊ ሽግግርና ዘላቂ ልማት ሊረጋገጥ የሚችለው በምርጫ ብቻ ነው። ሂደቱ የሁላችንም፣ ውጤቱ ደግሞ የኢትዮጵያ ነው!

#Ethiopia #Democracy #7thGeneralElections #NEBE #EthiopianBroadcastingCorporation