የማዕድን ዘርፍ ለብዙ ሀገራት በተለይም በተፈጥሮ ሀብት ለበለፀጉት የኢኮኖሚ ዕድገት ወሳኝ እና መሰረታዊ ሚና ይጫወታል።
ለሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪም ሆነ ለዓለም አቀፍ የአቅርቦት ሰንሰለቶች አስፈላጊ የሆኑ ጥሬ ዕቃዎችን በማቅረብ የሀብት፣ የሥራ ዕድል እና የውጭ ምንዛሪ ምንጭ ሆኖ ያገለግላል።
ይሁን እንጂ የሀገሮች ልምድ እንደሚያሳየው የማዕድን ሀብት ወደ ዘላቂ ልማት ገብቶ አዎንታዊ ትርጉም እንዲያመጣ ጠንካራ አስተዳደር እና ብዝኀ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ ላይ የተመሰረተ አመራር አስፈላጊ ነው፡፡
ዘርፉ በጥንቃቄ ከተያዘ ለሀገራት በረከትን ይዞ የሚመጣ ነው፡፡ እንደ ወርቅ፣ መዳብ እና የብረት ማዕድናት ያሉት የውጭ ምንዛሪ ምንጮች ናቸው።
ዘርፉ መጠነ ሰፊ እና ከፍተኛ ክፍያ የሚያስገኙ የሥራ ዕድልን ይፈጥራል። የአንድ ሀገርን ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ከ2 እስከ 5 እጥፍ የሚያነቃቃ ሲሆን፤ በመጓጓዣ፣ ኬተሪንግ፣ ሎጂስቲክስ እና ጥገና ላይ ቀጥተኛ ያልሆኑ የሥራ ዕድሎችን ይፈጥራል።
ዘላቂ የማዕድን ፕሮጀክቶች የመንገዶች፣ የባቡር ሀዲዶች፣ የወደቦች፣ የኃይል ማመንጫ ተቋማት እና የቴሌኮሙኒኬሽን መሰረተ ልማቶች እንዲስፋፉም ዕድል ይፈጥራል።
ለዘመናዊ ሕይወት እና ለኢንዱስትሪ ልማት፣ ለማኑፋክቸሪንግ፣ ለግንባታ እና ለኤሌክትሮኒክስ ምርት ማደግም ወሳኝ ሚና ይጫወታል፡፡
እንደ ሊቲየም፣ ኮባልት እና መዳብ ያሉት ማዕድናት ደግሞ በፍጥነት በማደግ ላይ ላለው አረንጓዴ ኢነርጂ ሽግግር ከፍተኛ ጠቀሜታ አላቸው፡፡
የማዕድን ሀብት በጥንቃቄ ከተመራ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያለው ነው፡፡ በታቃራኒው ሲሆን ደግሞ የትርምስ ምንጭ ሊሆን ይችላል፡፡
ማዕድንን በጥንቃቄ ለዕድገታቸው ከሚጠቀሙት ሀገራት መካከል ቦትስዋና በስኬታማ የማዕድን ልማቷ ትታወቃለች። 80 በመቶ የሚሆነው የቦትስዋና ኢኮኖሚ አልማዝን ወደ ውጭ በመላክ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡
ቦትስዋና በብዙ የአፍሪካ ሀገራት "የሀብት እርግማን" የሚባለውን የማዕድን ሀብት ላይ ያነጣጠረ የማያባራ ግጭትን ያስወገደ የስኬት ታሪክ እንዳላት ይነገራል። ይህም ሀገሪቱን በ1966 ከነበረችበት የከፋ ድህነት አውጥቶ ዘላቂ እና የተረጋጋ ከፍተኛ-መካከለኛ ገቢ ወዳላት ሀገር ለውጧታል።
አውስትራሊያ የብረት ማዕድን እና ሊትየም፤ ቺሊ ደግሞ የኮፐር እና ሊቲየም አምራቾች ሲሆኑ፤ ዘርፉን በጥንቃቄ በመምራት ለኢኮኖሚ ዕድገታቸው የተጠቀሙ ሀገራት ናቸው፡፡ የመንግሥትን እና የዜጎችን ጥቅም በማረጋገጥ የውጭ ኢንቨስትመንትን የሚስቡ ጠንካራ እና ግልጽ ስትራቴጂዎችን፣ እንዲሁም ጥብቅ ቁጥጥር እና የተጠኑ የፊስካል ማዕቀፎችን ተግባራዊ አድርገዋል።
ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በመዳብ፣ በኮባልት እና በወርቅ የበለፀገች ሲሆን፣ ማሊ ደግሞ በወርቅ ጥገኛ ነች። እነዚህ ሀገራት ግን ይህን ሰፊ የማዕድን ሀብታቸውን በሥርዓት ባለመጠቀማቸው ከበረከት ይልቅ እንደ እርግማን ተቆጥሮባቸው የትርምስ መንስኤ ሆኖባቸዋል።
በሀገራቱ ያለው ደካማ አስተዳደር፣ ሙስና፣ የፖለቲካ አለመረጋጋት እና ግጭት አብዛኛው የማዕድን ሀብታቸው እንዲባክን አድርጎታል። ከእነዚህ ሀገራት ከፍተኛ መጠን ያለው የማዕድን ምርት ወደ ውጭ ቢላክም የሀገራቱ መለያ ግን የከፋ ድህነት እና ግጭት ሆኖ ቀጥሏል፡፡
የኢኮኖሚ ሪፎርሙ ያነቃቃው የኢትዮጵያ የማዕድን ዘርፍ
ኢትዮጵያ ረዥም እና ጥንታዊ ማዕድን የማውጣት ታሪክ ቢኖራትም እስከ ኢሕአዴግ ያሉ መንግሥታት ዘርፉን በፖሊሲ ደግፈው ባለማዘመናቸው ከማዕድን ልታገኝበት የሚገባውን ጥቅም ሳታገኝ ቆይታለች።
ኢትዮጵያ በብረታ ብረት፣ በኢንዱስትሪ እና በኢነርጂ ማዕድናት የበለፀገች ብትሆንም ይህ ሀብቷ ሲባክን ኖሯል። በዓለም ላይ ካሉት ከፍተኛ ክምችቶች የሚመደበውን የዳነናክል ፖታሽ ክምችት እያላት ይህን ሀብቷን ተጠቅማ አንድም የማዳበሪያ ፋብሪካ ሳይኖራት እዚህ ደርሳለች፡፡ በፖታሽ ክምችት የምትታወቀው ሞሮኮ ግን በፖታሽ ሀብቷ ተጠቅማ ነው በአፍሪካ ከሚገኙ ማዳበሪያ አምራቾች አንዷ መሆን የቻለችው፡፡
ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ ብዝኀ ዘርፍን ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም እየተገበረ ያለው መንግሥት ማዕድንን ከአምስቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ምሰሶዎች (economic pillars) አንዱ አድርጎታል፡፡
ሪፎርሙ በዘርፉ ኢንቨስት ማድረግ ለሚፈልጉት ከመቼውም በላይ ምቹ ሁኔታን በመፍጠር የማዕድን ፍለጋን እና ማውጣትን ለማበረታታት እና ዘርፉን በሙሉ አቅም ለመጠቀም ዓላማ ያደረገ ነው።
በዘርፉ ለመሰማራት ለሚፈልጉ አካላት ምቹ የሕግ ማዕቀፍን ከማዘጋጀት ባለፈ እንደ የባቡር መንገድ፣ የመኪና መንገድ፣ የአየር ትራንስፖርት እና የኃይል መሰረተ ልማቶች ተሟልተዋል፡፡ የዘርፉን ችግሮችን ለመቅረፍም የማዕድን ካውንስል ተቋቁሞ ሥራ ጀምሯል፡፡
በዚህም መሰረት የማዕድን ዘርፍ ለ14 ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድልን በመፍጠር፣ 10 በመቶ የሀገር ውስጥ ገቢን እንዲሸፍን ታስቦ እንደሚሠራበት በ10 ዓመቱ የልማት ዕቅድ ሰነድ ላይ ተጠቅሷል፡፡
ከሪፎርሙ በኋላ ከምርት እና ገቢ አንጻር በወርቅ፣ በጌጣጌጥ ማዕድናት እና በሲሚንቶ ላይ የተመዘገቡት ለውጦች አበረታች እየሆኑ ይገኛል፡፡
በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የጥቁር ገበያ ችግርን በመቅረፍ በዘርፉ የተሰማሩ የወርቅ አቅራቢዎች ወርቅን ለብሔራዊ ባንክ እንዲያቀርቡ እየተደረገ ይገኛል፡፡
በዚህ ሂደት ያለፈው ሪፎርም አሁን ፍሬ እያፈራ የሚገኝ ሲሆን በ2017 በጀት ዓመት 37 ቶን ወርቅ ወደ ውጭ ተልኮ 3.5 ቢሊዮን ዶላር መገኘቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ለፓርላማ ባቀረቡት ሪፖርት ጠቅሰዋል።
አራት የወርቅ ፋብሪካዎችም እየተገነቡ ናቸው፡፡ የወርቅ ምርቱ እየጨመረ ሲሆን፣ በ2018 ዓ.ም ሩብ ዓመት ብቻ 11.4 ቶን ወርቅ ተመርቷል፡፡
ሌላው የዘርፉ ትሩፋት በሶማሊ ክልል የተገነባው በዓመት 111 ሚሊየን ሊትር ማምረት የሚችለው የኦጋዴን ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ ፕሮጀክት ሲሆን፣ በተደረገው ጥናትም ኢትዮጵያ 21 ትሪሊዮን ኪዩቢክ የጋዝ ክምችት እንዳላት ተረጋግጧል፡፡
የመጀመሪያው ዙር የጋዝ ፕሮጀክት ሲመረቅም ሌላ በዓመት 3.3 ቢሊዮን ሊትር የሚያመርት የተፈጥሮ ጋዝ ማጣሪያ ፕሮጀክት ፋብሪካ መሰረት ድንጋይ ተቀምጧል፡፡
የተፈጥሮ ጋዝ ፕሮጀክቱ ባለፈም ለማዳበሪያ ፋብሪካ ግብዓትነትም የሚውል በመሆኑ ትልቁ የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች ራስ ምታት የሆነው የማዳበሪያ ፋብሪካ መሰረት ድንጋይ ተቀምጧል።
ለዚህም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በቅርቡ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡት ሪፖርት ይህን ሀብት ለምን አልተጠቀምንም ብሎ መቆጨት ብቻ ሳይሆን አውቆ ለመጠቀም መሥራትን ዓላማ በማድረግ የፖሊሲ ማሻሻ መደረጉን የገለጹት።
ሌላው የዘርፉ ሪፎርም ውጤት የሆነው የሲሚንቶ የማምረት አቅምን በዓመት ወደ 20 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ማድረስ መቻሉ ነው፡፡ በዚህም በአንድ ወቅት በሀሪቱ ውስጥ አነጋጋሪ የነበረው የሲሚንቶ እጥረት በመፍታት ገበያውን ማረጋጋት ተችሏል፡፡
በለሚ ታደሰ