አዋሽ ባንክ ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የዲጂታል የብድር አገልግሎት ማቅረብ የሚያስችል 'መስመር ዲጂታል ሌንዲንግ' የተሰኘ ሥርዓት ይፋ አድርጓል።
ባንኩ ከማስተር ካርድ ፋውንዴሽን እና ፈርስት ኮንሰልት ጋር በመተባበር ይፋ ያደረገው አገልግሎቱ የቀረበው በአዋሽ ብር ፕሮ መተግበሪያ ውስጥ ነው።
ይህ ሥርዓት ይፋ የተደረገው በኢንተርፕራይዞች በኩል የሚታየውን የፋይናንስ ችግር ለመቅረፍ፣ የባንክ ሥርዓት ውስጥ ያልተካተቱትን ወደ ዘርፉ እንዲገቡ ለማስቻል እና ተደራሽነትን ለማስፋት መሆኑን በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ ተነግሯል።
በብድር አገልግሎቱ በተለይም ወጣቶች እና ሴቶች የሚበረታቱ መሆኑ የተነገረ ሲሆን፣ ዲጂታል ብድር አቅርቦቱን ኢንተርፕራይዞች ተጠቅመው ጊዜያቸውን በመቆጠብ ምርት እና ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚችሉ ተነግሯል።
ከዚህ ቀደም ተቋማቱ በጋራ በመሆን ''መስመር'' በተሰኘው የብድር ሥርዓት ላለፉት ሦስት ዓመታት፣ ከ13 ሺህ በላይ ለሚሆኑ አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች በድምሩ ከ1.3 ቢሊዮን ብር የብድር አገልግሎት ሰጥቷል ተብሏል።
ከእነዚህ የብድር አገልግሎት ተጠቃሚዎች ውስጥ 32 በመቶው ሴት ኢንተርፕራይዞች መሆናቸው በማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ተገልጿል።
በመርሐ ግብሩ የአዋሽ ባንክ ሲኒየር ቺፍ ማርኬቲንግ ኦፊሰር ዮሐንስ መርጊያ፣ የማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ካንትሪ ዳይሬክተር መፍትሄ ታደሰ፣ የፈርስት ኮንሰልት የመስመር አገልግሎት ኃላፊ ቀኖ ኢታና እና ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።
በብሩክታዊት አስራት