የሥልጣኔያችን እና የማንነታችን መገለጫ የሆኑት የጎንደር አብያተ-መንግሥት እድሳት ፋይዳው ትልቅ ነው ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ።
የጎንደር አብያተ-መንግሥት ከ400 ዓመታት በላይ የቆዩ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ከሥልጣኔ አኳያ ዘመኑ በኢትዮጵያ የመንገድ እና የድልድዮች ግንባታ ጅማሮም የታየበት እንደሆነ አክለዋል።

በሌላ በኩል ለበርካታ ዓመታት ግንባታው ሲጓተት የቆየው የመገጭ የመስኖ ግድብ የለውጡ መንግሥት በሰጠው ልዩ ትኩረት እና አዲስ አመራር አሁን በጥሩ ሂደት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ የአካባቢውን አርሶ አደሮች የመስኖ ልማት ተጠቃሚ ከማድረግ በተጨማሪ ለጎንደር የተጨማሪ ውኃ አቅርቦት ምንጭ እንደሚሆን አብራርተዋል።
ግድቡ የሚፈጥረው ሰው ሠራሽ ሐይቅም ተጨማሪ የቱሪስት መስህብ በመሆን እንደሚያገለግል ገልጸዋል።
ለኢትዮጵያ ከተሞች ትንሳዔ ምክንያት እየሆነ ባለው የኮሪደር ልማት ጎንደርም ለነዋሪዎቿ ምቹ እንዲሁም ለጎብኚዎች ሳቢ እየሆነች ትገኛለች ያሉት አቶ አረጋ፤ በፍጥነት እና በጥራት እየተከናወነ ያለው የአዘዞ መንገድ ግንባታም ሲጠናቀቅ የከተማዋን የትራፊክ እንቅስቃሴ እንደሚያሳልጠው አክለዋል።
በጥቅሉ በጎንደር እና ዙሪያዋ እየተከናወነ ያለው ልማት የከተማዋን የቱሪዝም እና የንግድ ዘርፎች እያነቃቃ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።
በሜሮን ንብረት
#ebcdotstream #Gondar #fasil #megech #corridor