በግንባታው ዘርፍ እውን ይሆናሉ ተብለው የማይገመቱ፣ ነገር ግን በተግባር ተገንብተው የሚታዩ ሥራዎች “ድንቅ የግንባታ ጥበብ” (Engineering Marvel) የሚል ስያሜ ይሰጣቸዋል።
ውስብስብ በሆነ መልክዓ-ምድር ላይ መገንባታቸው፣ የግንባታው ግዝፈትና ዲዛይን፣ የሚበረክቱት ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እንዲሁም ከአረንጓዴ ኢኮኖሚ ጋር ያላቸው ቁርኝት ግንባታዎቹን ድንቅ ከሚያስብላቸው መመዘኛዎች መካከል ተጠቃሾቹ ናቸው።
በድንቅ የግንባታ ጥበብ እውን ሆኖ ከአፍሪካ ቀዳሚ፣ ከዓለም ደግሞ ከ20ዎቹ ግዙፍ የኃይል ማመንጫ ግድቦች አንዱ ለመሆን የበቃው ታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብም ከኃይል ማመንጫነት ግቡ ባሻገር በርካታ ድልብ የሆኑ ጥቅሞችን የያዘ ፕሮጀክት ነው።
ጥናቶች እንደሚያመለክቱት፣ በዓለማችን ላይ ከሚፈጠሩ የሥራ ዕድሎች 10 በመቶ የሚሆነው በቱሪዝም ዘርፍ የሚገኝ ነው። በመጪዎቹ 10 ዓመታትም ከሚፈጠሩ ሦስት አዳዲስ የሥራ ዕድሎች መካከል አንዱ ከዚሁ ዘርፍ እንደሚሆን ይገመታል።
ኅዳሴ ግድብም ከታዳሽ ኃይል ማመንጨት ባለፈ በቱሪዝም ዘርፍ ዳጎስ ያለ ተጠቃሚነትን የሚያስገኝ ፕሮጀክት መሆኑን ከወዲሁ እያሳየ ነው።
በተለይም ግድቡ የፈጠረው ንጋት የተሰኘው ሰው ሠራሽ ሐይቅ ያስገኘው የውኃ ሀብትና የዓሣ ምርታማነት ለዘርፉ ዕድገት ትልቅ ዕድል ፈጥሯል። ይህንንም ለቱሪዝም ልማት ማዋል እንዲቻል ፍኖተ-ካርታ ተዘጋጅቶ መጠናቀቁ ተገልጿል።
ፍኖተ-ካርታው በሐይቁ ላይ በሚገነቡ ደሴቶች፣ በዙሪያው የሚያስፈልጉ የትራንስፖርት አቅርቦቶችና አማራጮች ላይ ያተኮረ መሆኑን “ኅዳሴ ለኢትዮጵያ ማንሰራራት” በሚል መሪ ቃል በጉባ በተዘጋጀው መድረክ ላይ የቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ስለሺ ግርማ ገልጸዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው፤ ኅዳሴን ከኃይል ማመንጫነት ባሻገር ለትምህርት፣ ለቱሪዝም፣ ለጥበብ ዘርፍ እና ለዓለም አቀፍ የልምድ ልውውጥ መጠቀም እንደሚቻል አመላክተዋል።
በኢትዮጵያውያን ላብና ጥረት የተገነባው ግድቡ፣ ለዲያስፖራ ቱሪዝም መጎልበትም ጉልህ ድርሻ እንደሚኖረው ተጠቁሟል። ከሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ባለፈ፣ በአህጉራዊ ደረጃ ግድቡን ለመጎብኘት ከፍተኛ ፍላጎት መኖሩን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ጎብኚዎች መጥተው የተራዘመ ቆይታ እንዲኖራቸው የሚያስችል ምቹ ከባቢ እየተፈጠረ መሆኑንም ተናግረዋል።
በዚህም በዓለም አቀፍ ደረጃ በጥራቱና በአገልግሎቱ ተወዳዳሪ የሆነ የቱሪዝም መዳረሻ በኅዳሴ ግድብ ዙሪያ እንደሚገነባ ሚኒስትር ዴኤታው አረጋግጠዋል።
በአፎሚያ ክበበው