ዛሬ የሚኤሶ - ድሬዳዋ የፍጥነት መንገድ ፕሮጀክት የሚገኝበትን የሥራ ሂደት በተመለከተ ከሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊዎች ጋር ውይይት አካሂደናል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
በፕሮጀክቱ የሥራ ሂደት እየተከናወኑ የሚገኙ የሰው ኃይል ዝግጅት፣ የማሽነሪና ሌሎች የግንባታ ዕቃዎች አቅርቦት፣ የመስክ ዝግጅት እና ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር የተደረጉ ውይይቶች ምን ይመስላሉ የሚሉትን አይተናል ብለዋል።
የሚኤሶ - ድሬዳዋ የፍጥነት መንገድ ፕሮጀክት ለከባድ የጭነት መኪኖች አዳጋች የነበረውን መንገድ ምቹ በማድረግ፣ የወጪና ገቢ ንግድን እንደሚያቀላጥፍ በማኅበራዊ የትስስር ገጽ ላይ ያሰፈሩት አቶ ተመስገን ጥሩነህ፤ በቀጣናዊ ትስስር ረገድ ያለንን ሚናም ያጎለብታል ሲሉ ጠቁመዋል።
ፕሮጀክቱ የኢኮኖሚያችንን ተወዳዳሪነትና የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል ጉልህ አበርክቶ የሚኖረው በመሆኑ በተያዘለት እቅድ መሠረት እንዲጠናቀቅ የተቀናጀ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ አቶ ተመስገን አሳስበዋል።