የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት እና የፓርቲው ዋናው ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ እንዳስታወቁት፤ "በመደመር መንግሥት ዕይታ፣ የዘርፎች እመርታ" በሚል መሪ ሀሳብ ለብልፅግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ከጥቅምት 19 እስከ 30 በአዳማ ከተማ እና በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ሲሰጥ የቆየው ስልጠና የብልፅግና ፓርቲ ፕሬዚዳንት ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሰጡት የሥራ መመሪያ ዛሬ በስኬት ፍፃሜውን አግኝቷል።
ከመላው ኢትዮጵያ የተውጣጡ ወደ 2000 የሚጠጉ የፓርቲው አመራሮች የተሳተፉበትና የአስተሳሰብ አንድነት ከመፍጠርና የተግባር አፈፃፀምን ከማላቅ አኳያ እጅግ ከፍተኛ ፋይዳ በተገኘበት በዚህ ስልጠና ፓርቲው እውነተኛ የኅብረ ብሔራዊነት ተምሳሌት መሆኑም በተጨባጭ የተንፀባረቀበት ነበር ሲሉም ገልጸዋል።

የስልጠና መርሀ ግብሩ ከዝግጅት እስከ ገለፃ፣ የቡድን ውይይት፣ ተሞክሮ ልውውጥ፣ የልማት ሥራዎች የመስክ ጉብኝት እና ማጠቃለያ ድረስ ዓላማውን በሚገባ አሳክቶ እንዲጠናቀቅ ኃላፊነታችሁን ለተወጣችሁ አስተባባሪዎች፣ አሰልጣኞች፣ አወያዮች፣ የፀጥታ ተቋማት፣ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት እና ልዩ ልዩ ተቋማቱ፣ የአዳማ ከተማ አስተዳደር፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና የስልጠናው ተሳታፊ አመራሮች በሙሉ ላበረከታችሁት ከፍተኛ አስተዋፅዖ በብልፅግና ፓርቲ ስም ልባዊ ምስጋና ለማቅረብ እወዳለሁ ብለዋል አቶ አደም ፋራህ በመልዕክታቸው።